ሕዝቅኤል 29:3-9 NASV

3 እንዲህም ብለህ ተናገረው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።“ ‘በወንዞችህ መካከል የምትተኛ አንተ ታላቅ አውሬ፣የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ።“የዐባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ለራሴም ሠርቼዋለሁ” ትላለህ።

4 ነገር ግን በመንጋጋህ መንጠቆ አስገባለሁ፤የወንዞችህን ዓሦች ከቅርፊትህ ጋር አጣብቃለሁ፤ቅርፊትህ ላይ ከተጣበቁት ዓሦች ሁሉ ጋር፣ከወንዞችህ ጐትቼ አወጣሃለሁ።

5 አንተንና በወንዞችህ ያለውን ዓሣ ሁሉ፣በምድረ በዳ እጥላለሁ።በገላጣ መሬት ላይ ትወድቃለህ፤የሚሰበስብህ፣ የሚያነሣህም አይኖርም።ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች፣ምግብ እንድትሆን አሳልፌ እሰጥሃለሁ።

6 ከዚያም በግብፅ የሚኖሩ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።“ ‘ለእስራኤል ቤት የሸምበቆ በትር ነበርህ፤

7 በእጃቸው ሲይዙህ ተሰንጥረህ ትከሻቸውን ወጋህ፤ ሲደገፉህም ተሰብረህ ጀርባቸውን አጐበጥህ።

8 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፤ ሰዎችህንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ።

9 ግብፅ ባድማና ምድረ በዳ ትሆናለች፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።“ ‘የዐባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ እኔም ሠርቼዋለሁ” ብለሃልና፤