ሕዝቅኤል
ምዕራፎች 3:22-27
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
22 የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም፣ “ተነሥተህ ወደ ረባዳው ስፍራ ሂድ፤ በዚያ እናገርሃለሁ” አለኝ።
23እኔም ተነሥቼ ወደ ረባዳው ስፍራ ሄድሁ። በኮቦር ወንዝ አጠገብ ያየሁት ዐይነት ክብር፣ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ።
24መንፈስ በውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ እንዲህም ሲል ተናገረኝ፤ “ሂድ፤ ቤትህ ገብተህ በርህን ዝጋ።
25አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ በገመድ ይጠፍሩሃል፤ ወጥተህም በሕዝብ መካከል እንዳትመላለስ ያስሩሃል።
26ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም ልትገሥጻቸው እንዳትችል ምላስህን ከላንቃህ ጋር አጣብቃለሁ፤ ድዳም ትሆናለህ።
27ነገር ግን በምናገርህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፤ አንተም፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ትላቸዋለህ። የሚሰማ ይስማ፤ የማይሰማም አይስማ፤ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና።