ሕዝቅኤል 32:25-31 NASV

25 በመቃብሯ ዙሪያ ካለው መላው ሰራዊቷ ጋር፣ በታረዱት መካከል መኝታ ተዘጋጅቶላታል። ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ ሽብራቸው በሕያዋን ምድር ስለ ተነዛ፣ ወደ ጒድጓድ ከሚወርዱት ጋር ዕፍረታቸውን ይሸከማሉ፤ በታረዱትም መካከል ይጋደማሉ።

26 “ሞሳህና ቶቤል መቃብሮቻቸው በብዙ ሰራዊታቸው መቃብር ተከበው ይገኛሉ፤ ሁሉም ያልተገረዙ ሲሆኑ፣ በሕያዋን ምድር ሽብራቸውን ስለነዙ በሰይፍ ተገድለዋል።

27 ከዘመናት በፊት ከወደቁት ከኀያላን ሰዎች፣ ከእነዚያ ሰይፋቸውን ተንተርሰው፣ ጋሻቸውንም ደረታቸው ላይ ይዘው ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ መቃብር ከወረዱት ጋር አይጋደሙምን? የእነዚህ ተዋጊዎች ሽብር በሕያዋን ምድር ባሉት ኀያላን ላይ ቢደርስም የኀጢአታቸው ቅጣት በዐጥንታቸው ላይ ይሆናል።

28 “ፈርዖን ሆይ፤ አንተም እንደዚሁ ትሰበራለህ፤ በሰይፍ ከተገደሉት ከእነዚያ ካልተገረዙት ጋር ትጋደማለህ።

29 “ኤዶምም በዚያ አለች፤ ንጉሦቿና ገዦቿም ሁሉ በዚያ አሉ፤ ኀይል የነበራቸው ቢሆኑም፣ በሰይፍ ከተገደሉት ጋር ተጋድመዋል፤ ወደ ጒድጓድ ከወረዱት ከእነዚያ ካልተገረዙትም ጋር ተኝተዋል።

30 “የሰሜን ገዦች በሙሉ፣ ሲዶናውያንም ሁሉ በዚያ ይገኛሉ፤ ከዚህ በፊት በኀይላቸው ምክንያት ሽብር የፈጠሩ ቢሆኑም፣ ከታረዱት ጋር በኀፍረት ወረዱ፤ ሳይገረዙም በሰይፍ ከተገደሉት ጋር ይጋደማሉ፤ ወደ ጒድጓድ ከወረዱትም ጋር ኀፍረታቸውን ይሸከማሉ።

31 “ፈርዖንና ሰራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል፤ በሰይፍ ከተገደለበት ሰራዊትም ሁሉ ሐዘን ይጽናናል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።