ሕዝቅኤል 33:19-25 NASV

19 ክፉም ሰው ከክፉ ሥራው ተመልሶ ቀናውንና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ፣ ይህን በማድረጉ በሕይወት ይኖራል።

20 ይሁን እንጂ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ፤ ነገር ግን በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።”

21 በተማረክን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን፣ ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፣ “ከተማዪቱ ወደቀች!” አለኝ።

22 ሰውየው ከመድረሱ በፊት በነበረው ምሽት፣ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ላይ ነበረች፤ በማለዳም ሰውየው ወደ እኔ ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሔር አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተ፤ ከዚያ በኋላ ዝም አላልሁም።

23 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

24 “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር በፍርስራሾች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ ‘አብርሃም አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ ያም ሆኖ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ግን ብዙዎች ነን፤ በእርግጥ ምድሪቱ ርስት ሆና ተሰጥታናለች’ ይላሉ።

25 ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሥጋውን ከነደሙ ትበላላችሁ፤ ዐይኖቻችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፤ ደምም ታፈሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ታስባላችሁ?