ሕዝቅኤል 34:10-16 NASV

10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በእረኞች ላይ ተነሥቻለሁ፤ ስለ መንጋዬ እጠይቃቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ እረኞች ራሳቸውን መመገብ እንዳይችሉ፣ መንጋዬን እንዳያሰማሩ አደርጋለሁ። መንጋዬን ከአፋቸው አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህም ምግብ አይሆናቸውም።

11 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋቸዋለሁ፤ እጠብቃቸዋለሁም።

12 እረኛ ከመንጋው ጋር ሳለ፣ የተበተኑበትን በጎች እንደሚፈልግ ሁሉ፣ እኔም በጎቼን እፈልጋለሁ። በደመናና በጨለማቀን ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ።

13 ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ።

14 በመልካሙ ስፍራ አሰማራቸዋለሁ፤ የእስራኤል ተራሮች ከፍታም የግጦሽ መሬት ይሆናቸዋል። በመልካሙ ግጦሽ መሬት ላይ ይተኛሉ፤ እዚያም በእስራኤል ተራሮች ለምለም መስክ ላይ ይመገባሉ።

15 እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፤ አስመስጋቸዋለሁም። ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

16 የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን ግን አጠፋለሁ። መንጋውን በፍትሕ እጠብቃለሁ።