20 የጻፍህባቸውን በትሮች ከፊት ለፊታቸው ያዝ፤
21 እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስራኤላውያንን ከሄዱባቸው አሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየስፍራው ሰብስቤ ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
22 በምድሪቱ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፤ በሁሉም ላይ አንድ ንጉሥ ይነግሣል፤ ከእንግዲህም ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፤ መንግሥታቸውም ከሁለት አይከፈልም።
23 በጣዖታቶቻቸው፣ በአስጸያፊ ምስሎቻቸው ወይም በማንኛውም ኀጢአት ራሳቸውን አያረክሱም፤ ነገር ግን እኔን በመተው ከሠሩት ኀጢአት ሁሉ አድናቸዋለሁ፤ አነጻቸዋለሁም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።”
24 “ ‘ባሪያዬ ዳዊት በላያቸው ይነግሣል፤ ሁሉም አንድ እረኛ ይኖራቸዋል፤ ሕጌን ይከተላሉ፤ ሥርዐቴንም በጥንቃቄ ይጠብቃሉ።
25 አባቶቻችሁ በኖሩበት፣ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠሁት ምድር ይኖራሉ። በዚያም እነርሱ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘላለም ይኖራሉ፤ ባሪያዬ ዳዊትም ለዘላለም ንጉሣቸው ይሆናል።
26 ከእነርሱም ጋር የሰላም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ቃል ኪዳኑም የዘላለም ይሆናል። አጸናቸዋለሁ፤ አበዛቸዋለሁ፤ መቅደሴንም በመካከላቸው ለዘላለም አኖራለሁ።