ሕዝቅኤል 38:12-18 NASV

12 እዘርፋለሁ፤ እነጥቃለሁ፤ እንዲሁም ከአሕዛብ ተሰባስቦ እንደ ገና በሰፈረው፣ በከብትና በሸቀጥ በከበረው፣ በምድሪቱም መካከል በሚኖረው ሕዝብ ላይ እጄን አነሣለሁ።”

13 ሳባና ድዳን፣ የተርሴስ ነጋዴዎችና መንደሮቿም ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፤ “ልትዘርፍ መጣህን? ሰራዊትህን ያሰባሰብኸው ለመበዝበዝ፣ ወርቅና ብሩን አጋብሶ ለመሄድ፣ ከብቱንና ሸቀጡን ለመውሰድ፣ ብዙ ምርኮ ይዞ ለመመለስ ነውን?” ’

14 “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ ጎግንም እንዲህ በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል በሰላም መቀመጡን ዐውቀህ አትንቀሳቀስምን?

15 በስተ ሰሜን ርቆ ከሚገኘው ቦታ ትመጣለህ፤ አንተና ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝቦች፣ እጅግ ታላቅ ኀያል ሰራዊትም በፈረሶች ላይ ሆናችሁ ትመጣላችሁ።

16 ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ሆነህ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፤ በፊታቸው ቅድስናዬን ስገልጥ ሕዝቦች እኔን ያውቁ ዘንድ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።”

17 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በቀደመው ዘመን በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያት ስለ እርሱ የተናገርሁለት ያ ሰው አንተ አይደለህምን? በዚያን ወቅት አንተን በእነርሱ ላይ እንደማመጣባቸው ለብዙ ዓመታት ትንቢት ተናገሩ።”

18 በዚያን ጊዜ እንዲህ ይሆናል፤ “ጎግ የእስራኤልን ምድር ሲወጋ፣ ብርቱ ቍጣዬ ይነሣሣል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።