ሕዝቅኤል 38:16-22 NASV

16 ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ሆነህ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፤ በፊታቸው ቅድስናዬን ስገልጥ ሕዝቦች እኔን ያውቁ ዘንድ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።”

17 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በቀደመው ዘመን በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያት ስለ እርሱ የተናገርሁለት ያ ሰው አንተ አይደለህምን? በዚያን ወቅት አንተን በእነርሱ ላይ እንደማመጣባቸው ለብዙ ዓመታት ትንቢት ተናገሩ።”

18 በዚያን ጊዜ እንዲህ ይሆናል፤ “ጎግ የእስራኤልን ምድር ሲወጋ፣ ብርቱ ቍጣዬ ይነሣሣል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

19 በዚያን ጊዜ በቅናቴና በሚያስፈራው ቍጣዬ በእስራኤል ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ይሆናል ብዬ ተናግሬአለሁ።

20 የባሕር ዓሦች፣ የሰማይ ወፎች፣ የምድር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚሳብ ማንኛውም ፍጡር፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ፣ በፊቴ ይንቀጠቀጣሉ፤ ተራሮች ይገለባበጣሉ፤ ገደሎች ይናዳሉ፤

21 በተራሮቼም ሁሉ በጎግ ላይ ሰይፍ እጠራለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእያንዳንዱም ሰው ሰይፍ በወንድሙ ላይ ያርፋል።

22 በቸነፈርና በደም መፋሰስ እፈርድበታለሁ፤ የዝናብ ዶፍ፣ የበረዶ ድንጋይ፣ የሚያቃጥል ድኝ፣ በእርሱና በወታደሮቹ፣ ከእርሱም ጋር ባሉት ሕዝቦች ላይ አወርዳለሁ።