ሕዝቅኤል 4:1-7 NASV

1 “አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ የሸክላ ጡብ ወስደህ ከፊት ለፊትህ አስቀምጥ፤ የኢየሩሳሌምን ከተማ ካርታ ሥራበት።

2 ከዚያም በወታደር እንደሚከበብ ክበባት፤ ምሽግ ሥራባት፤ ዐፈር ደልድልባት፤ ጦር ሰፈሮችን ቀብቅብባት፤ ቅጥር መደርመሻ ግንዶችንም በዙሪያዋ አስቀምጥባት።

3 የብረት ምጣድ ወስደህ በአንተና በከተማዪቱ መካከል እንደ ብረት ቅጥር አቁመው፤ ፊትህንም ወደ እርሷ አዙር፤ የተከበበች ትሆናለች፤ አንተም ትከባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።

4 “አንተ በግራ ጐንህ ተኛ፤ የእስራኤልም ቤት ኀጢአት በአንተ ላይ ይሁን፤ በዚህ ጐንህ በተኛህበት ቀን ቊጥር ኀጢአታቸውን ትሸከማለህ።

5 እነርሱ ኀጢአት ባደረጉባቸው ዓመታት መጠን የቀን ቊጥር መድቤብሃለሁ። ስለዚህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን የእስራኤልን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ።

6 “ይህን ከፈጸምህ በኋላ ደግሞ በቀኝ ጐንህ ተኝተህ የይሁዳን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ፤ ለእያንዳንዱ ዓመት አንድ አንድ ቀን በማድረግ አርባ ቀን መድቤብሃለሁ።

7 ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ታዞራለህ፣ በራቍት ክንድህ ትንቢት ተናገርባት።