ሕዝቅኤል 43:14-20 NASV

14 ከቦዩ መሠረት አንሥቶ እስከታችኛው ዕርከን ድረስ ሁለት ክንድ ቁመት፣ ሁለት ክንድ ወርድ ያለው ሲሆን፣ ከትንሹ ዕርከን አንሥቶ እስከ ትልቁ ዕርከን ድረስ ደግሞ አራት ክንድ ቁመት፣ አንድ ክንድ ወርድ አለው።

15 የመሠዊያው ምድጃ ከፍታው አራት ክንድ ሲሆን፣ ከምድጃው ወጣ ወጣ ያሉ አራት ቀንዶች አሉ።

16 የመሠዊያው ምድጃ እኩል በእኩል ሲሆን፣ ርዝመቱ ዐሥራ ሁለት ክንድ፣ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው።

17 ላይኛው ዕርከንም እንዲሁ እኩል በእኩል ሆኖ ዐሥራ አራት ክንድ ርዝመትና ዐሥራ አራት ክንድ ወርድ አለው፤ ግማሽ ክንድ ጠርዝና ዙሪያውን በሙሉ አንድ ክንድ የሆነ ቦይ ነበረው። የመሠዊያው ደረጃዎችም በምሥራቅ ትይዩ ናቸው።”

18 ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መሠዊያው ተሠርቶ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚሠዋበትና በመሠዊያው ላይ ደም በሚረጭበት ጊዜ ሥርዐቶቹ እነዚህ ናቸው፤”

19 በፊቴ ቀርበው ለሚያገለግሉኝ ካህናት፣ ለሌዋውያኑ ለሳዶቅ ቤተ ሰብ የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ስጥ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

20 ከደሙም ጥቂት ወስደህ፣ በመሠዊያው አራት ቀንዶች፣ በላይኛው ዕርከን አራት ጐኖች ላይ እንዲሁም በጠርዙ ዙሪያ ሁሉ ታደርጋለህ፤ በዚህ ሁኔታ መሠዊያውን ታነጻለህ፤ ታስተሰርይለታለህም።