ሕዝቅኤል 45:7-13 NASV

7 ‘ “ገዡ ከቅዱሱ ስፍራና ከከተማው ወሰን ግራና ቀኝ ርስት ይኖረዋል፤ ይህም ከምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ምሥራቅ በመዝለቅ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያለውን ወሰን ርዝመት ተከትሎ ለአንዱ ነገድ ከተሰጠው ርስት ጋር ጐን ለጐን ይሄዳል።

8 ይህም መሬት በእስራኤል ምድር የገዡ ርስት ይሆናል። ከእንግዲህ ገዦቼ ሕዝቤን አይጨቍኑም፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት በየነገዳቸው ርስት እንዲይዙ ይፈቅዱላቸዋል።

9 ‘ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእስራኤል ገዦች ሆይ! ከልክ ዐልፋችኋል፤ ይብቃችሁ፤ ዐመፅንና ጭቈናን ተዉ፤ ቀናና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ። የሕዝቤን ርስት መቀማት ይቅርባችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

10 ትክክለኛ ሚዛን ትክክለኛ ኢፍና ትክክለኛ ባዶስ ይኑራችሁ።

11 የኢፍና የባዶሱ መመዘኛ ተመሳሳይ ይሁን፤ አንድ ባዶስ የሆመር አንድ ዐሥረኛ እንዲሁም አንድ ኢፍ የሆመር አንድ ዐሥረኛ ይሆናል፤ ሆመር ለሁለቱም ሚዛኖች መደበኛ መለኪያ ነው።

12 አንድ ሰቅል ሃያ ጌራህ የሚይዝ ይሆናል፤ በሃያ ሰቅል ላይ ሃያ አምስት ሰቅልና ዐሥራ አምስት ሰቅል ሲጨመር አንድ ምናን ይሆናል።’

13 ‘ “የምታቀርቡት ልዩ መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ሆመር መስፈሪያ ስንዴ አንድ ስድስተኛ ኢፍ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ሆመር ገብስ አንድ ስድስተኛ ኢፍ ነው።