ሕዝቅኤል 47:3-9 NASV

3 ያም ሰው የመለኪያውን ገመድ በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ በመሄድ፣ አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ ከዚያም እስከ ቁርጭምጭሚት በሚደርሰው ውሃ ውስጥ መራኝ፤

4 ቀጥሎም አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ እስከ ጒልበት ወደሚደርስም ውሃ መራኝ፤ ከዚያም ሌላ አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ እስከ ወገብ ወደሚደርስም ውሃ መራኝ።

5 እንደ ገናም አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ አሁን ግን ልሻገረው የማልችል ወንዝ ሆነ፤ ምክንያቱም ውሃው ስለ ሞላና ጥልቅ ስለ ነበረ፣ በዋና ካልሆነ በስተቀር በእግር ሊሻገሩት የማይቻል ነበረ።

6 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን ታየዋለህን?” ሲል ጠየቀኝ።ከዚያም መልሶ ወደ ወንዙ ዳር መራኝ፤

7 እዚያም በደረስሁ ጊዜ፣ በወንዙ ግራና ቀኝ ብዙ ዛፍ አየሁ።

8 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ይህ ውሃ ወደ ምሥራቅ ምድር ይፈሳል፤ ወደ ባሕሩ ወደሚገባበት ወደ ዓረባ ይወርዳል፤ ወደ ባሕሩም ሲፈስ፣ በዚያ የነበረው ውሃ ንጹሕ ይሆናል።

9 ወንዙ በሚፈስበት ስፍራ ሁሉ ብዙ ሕያዋን ፍጡራን ይኖራሉ። ይህ ውሃ በዚያ ስለሚፈስና ጨውማ የሆነውን ውሃ ንጹሕ ስለሚያደርገው፣ ዓሣ በብዛት ይኖራል፤ ስለዚህ ወንዙ በሚፈስበት ስፍራ ሁሉ ማንኛውም ነገር በሕይወት ይኖራል።