ኤርምያስ 14:7-13 NASV

7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአንተ መኰብለል አብዝተናል፤በአንተም ላይ ዐምፀናል፤ኀጢአታችን ቢመሰክርብንም እንኳ፣ስለ ስምህ ብለህ አንድ ነገር አድርግልን።

8 አንተ የእስራኤል ተስፋ፤በጭንቀት ጊዜ አዳኙ፣ለምን በምድሪቱ እንደ ባዕድ፣እንደ ሌት አዳሪ መንገደኛ ትሆናለህ?

9 ግራ እንደ ተጋባ ሰው፣ለመታደግም ኀይል እንዳጣ ተዋጊ ትሆናለህ? እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በመካከላችን አለህ፤በስምህም ተጠርተናል፤እባክህ አትተወን።

10 እግዚአብሔር ስለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፤“መቅበዝበዝ እጅግ ይወዳሉ፤እግሮቻቸው አይገቱም፤ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፤አሁን በደላቸውን ያስባል፤በኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።”

11 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ለዚህ ሕዝብ በጎነት አትጸልይ፤

12 ቢጾሙም ጩኸታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ቢያቀርቡም አልቀበላቸውም፤ ነገር ግን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር አጠፋቸዋለሁ።”

13 እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወዮ!፣ ነቢያቱ ‘ሰይፍ አታዩም፤ ራብም አያገኛችሁም፤ ነገር ግን በዚህ ስፍራ ዘለቄታ ያለው ሰላም እሰጣችኋለሁ’ ይላል ይሏቸዋል” አልሁ።