ኤርምያስ 15:1-7 NASV

1 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ሙሴና ሳሙኤል እንኳ በፊቴ ቢቆሙ፣ ልቤ ለዚህ ሕዝብ አይራራምና፤ ከፊቴ አስወጣቸው፤ ይሂዱ።

2 እነርሱም፣ ‘ወዴት እንሂድ?’ ቢሉህ፣ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ለሞት የተመደበ ወደ ሞት፣ለሰይፍ የተመደበ ወደ ሰይፍ፣ለራብ የተመደበ ወደ ራብ፣ለምርኮ የተመደበ ወደ ምርኮ ይሄዳል።’

3 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አራት ዐይነት አጥፊዎችን እሰድባቸዋለሁ፤ እነዚህም፦ ለመግደል ሰይፍ፣ ለመጐተት ውሾች፣ እንዲሁም ጠራርጎ ለመብላትና ለማጥፋት የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ናቸው።

4 የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ካደረገው በደል የተነሣ፣ ለምድር ነገሥታት ሁሉ መሰቀቂያ አደርጋቸዋለሁ።

5 “ኢየሩሳሌም ሆይ፤ የሚራራልሽ ማን ነው?ማንስ ያለቅስልሻል?ደኅንነትሽንስ ማን ጎራ ብሎ ይጠይቃል?

6 እኔን ጥለሽኛል” ይላል እግዚአብሔር፤“ወደ ኋላም እያፈገፈግሽ ነው፤ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ አጠፋሻለሁም፤ከእንግዲህም አልራራልሽም።

7 በአገሪቱ የከተማ ደጆች፣በመንሽ እበትናቸዋለሁ፤ከመንገዳቸው አልተመለሱምና፣ሕዝቤን በሐዘን እመታለሁ፤ጥፋትም አመጣባቸዋለሁ፤