ኤርምያስ 24:5-10 NASV

5 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፣ ከዚህ ስፍራ ወደ ባቢሎናውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳ ምርኮ በመልካም አስበዋለሁ።

6 ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።

7 እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹም ልባቸውም ወደ እኔ ስለሚመለሱ፣ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።

8 “ ‘ነገር ግን ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበላ እንደ ማይቻለው እንደ መጥፎ በለስ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና ባለሥልጣኖቹን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የቀሩትንም ሆነ በግብፅ የሚኖሩትን፣ እንዲሁ አደርግባቸዋለሁ።

9 በምድር መንግሥታት ሁሉ ፊት የሚያስጸይፉና የሚሰደቡ ይሆናሉ፤ በምበትናቸውም ስፍራ ሁሉ ለማላገጫና ለመተረቻ፣ ለመሣለቂያና ለርግማን አደርጋቸዋለሁ።

10 ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ ሰይፍ፣ ራብና መቅሠፍት እሰድባቸዋለሁ።