ኤርምያስ 25:28-34 NASV

28 ነገር ግን ጽዋውን ከእጅህ ለመውሰድና ለመጠጣት እንቢ ካሉ፣ እንዲህ በላቸው፦ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በግድ ትጠጣላችሁ።

29 እነሆ፤ ስሜ የተጠራበትን ከተማ ማጥፋት እጀምራለሁ፤ ታዲያ ያለ ቅጣት ታመልጣላችሁን? ሳትቀጡ አትለቀቁም፤ በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ሳትቀጡ አታመልጡም፤ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።’

30 “እንግዲህ ይህን ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገርባቸው፤ እንዲህም በላቸው፣“ ‘እግዚአብሔር ከላይ ይጮኻል፤ከቅዱስ ማደሪያው ነጐድጓዳማ ድምፁን ያሰማል፤በራሱ ምድር ላይ እጅግ ይጮኻል፤እንደ ወይን ጨማቂዎች፣በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይም ያስገመግማል፤

31 እግዚአብሔር ከሕዝቦች ጋር ይፋረዳልና፣ታላቅ ጩኸት እስከ ምድር ዳርቻ ያስተጋባል፤በሰው ሁሉ ላይ ፍርድን ያመጣል፤ክፉዎችንም ለሰይፍ ይዳርጋል”ይላል እግዚአብሔር።

32 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ ጥፋት፣ከአገር ወደ አገር እየተዛመተ መጥቶአል፤ብርቱ ዐውሎ ነፋስ፣ከምድር ዳርቻ ተነሥቶአል።

33 በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ፤ እንደ ጒድፍ በምድር ላይ ይጣላሉ እንጂ፣ አይለቀስላቸውም፤ ሬሳቸውም አይሰበሰብም፤ አይቀበርምም።

34 እናንት እረኞች፤ አልቅሱ፤ ዋይ በሉ፤እናንት የመንጋው ጌቶች፤ በዐመድ ላይ ተንከባለሉ፤የምትታረዱበት ቀን ደርሶአልና፤እንደ ውብ የሸክላ ዕቃ ወድቃችሁ ትከሰክሳላችሁ።