4 የይሁዳንም ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፣ ሌሎች ከይሁዳ ወደ ባቢሎን ተማርከው የተወሰዱትንም ሁሉ ወደዚህ ስፍራ እመልሳለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ የባቢሎን ንጉሥ የጫነባቸውን ቀንበር እሰብራለሁና።’ ”
5 ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት ቆመው በነበሩት ሕዝብ ሁሉ ፊት፣ ለነቢዩ ለሐናንያ እንዲህ ብሎ መለሰለት፦
6 “አሜን፤ እግዚአብሔር ያድርገው፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ፣ ተማርከው የተወሰዱትንም ምርኮኞች ሁሉ ከባቢሎን በመመለስ፣ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ቃል ይፈጽም።
7 ነገር ግን ለአንተም ለዚህም ሕዝብ የምናገረውን ቃል ስማ፤
8 ከአንተና ከእኔ በፊት ጥንት የተነሡ ነቢያት፣ በብዙ አገሮችና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ጦርነት፣ ስለ ጥፋትና ስለ መቅሠፍት ትንቢት ተናግረዋል።
9 ነገር ግን ስለ ሰላም ትንቢት የተናገረ ነቢይ እግዚአብሔር በእውነት እንደላከው የሚታወቀው የተናገረው ትንቢት ሲፈጸም ነው።
10 ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ኤርምያስ ዐንገት ወስዶ ሰበረው፤