ኤርምያስ 28:8-14 NASV

8 ከአንተና ከእኔ በፊት ጥንት የተነሡ ነቢያት፣ በብዙ አገሮችና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ጦርነት፣ ስለ ጥፋትና ስለ መቅሠፍት ትንቢት ተናግረዋል።

9 ነገር ግን ስለ ሰላም ትንቢት የተናገረ ነቢይ እግዚአብሔር በእውነት እንደላከው የሚታወቀው የተናገረው ትንቢት ሲፈጸም ነው።

10 ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ኤርምያስ ዐንገት ወስዶ ሰበረው፤

11 በሕዝቡም ፊት፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የና ቡከደናፆርን ቀንበር ከሕዝቡ ሁሉ ጫንቃ ላይ ልክ እንደዚህ እሰብራለሁ’ አለ። በዚህ ጊዜ፣ ነቢዩ ኤርምያስ ትቶት መንገዱን ቀጠለ።

12 ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ከሰበረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

13 “ሄደህ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አንተ የዕንጨት ቀንበር ሰብረሃል፤ እኔ ግን በምትኩ የብረት ቀንበር እሠራለሁ።

14 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እንዲያገለግሉ፣ በእነዚህ ሕዝቦች ላይ የብረት ቀንበር አደርጋለሁ፤ እነርሱም ይገዙለታል፤ በዱር አራዊት ላይ እንኳ ሥልጣን እሰጠዋለሁ።’ ”