ኤርምያስ 3:12-18 NASV

12 ሂድና ይህን መልእክት ወደ ሰሜን እንዲህ ብለህ ተናገር፤“ ‘ከዳተኛዪቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሽ’ ይላል እግዚአብሔር፤‘እኔ መሓሪ ስለ ሆንሁ፣ከእንግዲህ በቍጣ ዐይን አላይሽም’ይላል እግዚአብሔር። ‘ለዘላለም አልቈጣም።

13 በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅሽ፣ክብርሽንም ለእንግዶች አማልክት፣በየለምለሙ ዛፍ ሥር አሳልፈሽ በመስጠት፣ለእኔ ባለመታዘዝሽ፣በደለኛ መሆንሽን ይህን አንድ ነገር ብቻ እመኚ’ ”ይላል እግዚአብሔር።

14 “ከዳተኛ ልጆች ሆይ፤ እኔ ባለቤታችሁ ነኝና ተመለሱ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከአንድ ከተማ አንድ፣ ከአንድ ነገድ ሁለት መርጫችሁ ወደ ጽዮን አመጣችኋለሁ።

15 እንደ ልቤም የሆኑ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የሚመሯችሁን እረኞች እሰጣችኋለሁ።

16 ቍጥራችሁ በምድሪቱ እጅግ በሚበዛበት ጊዜም ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚያ ዘመን፣ ‘የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት’ ብለው ከእንግዲህ አይጠሩም፤ ትዝ አይላቸውም፤ አያስታውሱትምም፤ አይጠፋም፤ ሌላም አይሠራም።

17 በዚያ ጊዜ ኢየሩሳሌምን፣ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ብለው ይጠሯታል፤ መንግሥታትም ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ለማክበር በኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ የክፉ ልባቸውንም እልኸኝነት ከእንግዲህ አይከተሉም።

18 በዚያን ዘመን የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት በአንድነት ሆነው ከሰሜን ምድር ለአባቶቻቸው ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይመጣሉ።