15 እንደ ልቤም የሆኑ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የሚመሯችሁን እረኞች እሰጣችኋለሁ።
16 ቍጥራችሁ በምድሪቱ እጅግ በሚበዛበት ጊዜም ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚያ ዘመን፣ ‘የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት’ ብለው ከእንግዲህ አይጠሩም፤ ትዝ አይላቸውም፤ አያስታውሱትምም፤ አይጠፋም፤ ሌላም አይሠራም።
17 በዚያ ጊዜ ኢየሩሳሌምን፣ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ብለው ይጠሯታል፤ መንግሥታትም ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ለማክበር በኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ የክፉ ልባቸውንም እልኸኝነት ከእንግዲህ አይከተሉም።
18 በዚያን ዘመን የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት በአንድነት ሆነው ከሰሜን ምድር ለአባቶቻቸው ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይመጣሉ።
19 “እኔም፣“ ‘የተመረጠችውን ምድር፣የትኛውም ሕዝብ ያላገኘውን የተዋበች ርስት ልሰጥሽ፣እንደ ወንዶች ልጆቼ ምንኛ በደስታ ልቍጠርሽ” አልሁ፤‘አባቴ’ ብለሽ የምትጠሪኝ፣እኔንም ከመከተል ዘወር የማትይ መስሎኝ ነበር።
20 የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለባሏ ታማኝ እንዳልሆነች ሚስት፣ስታታልሉኝ ኖራችኋል፤”ይላል እግዚአብሔር።
21 እግዚአብሔር አምላካቸውን በመርሳት፣መንገዳቸውን አጣመዋልና፣የእስራኤል ሕዝብ ጩኸት፣አሳዛኝ ልቅሶ ባድማ ከሆኑት ኰረብታዎች ተሰማ።