ኤርምያስ 39:11-17 NASV

11 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በክብር ዘበኞቹ አዛዥ በናቡዘረዳን በኩል ስለ ኤርምያስ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤

12 “ውሰደውና እንክብካቤ አድርግለት፤ የሚፈልገውን ነገር ፈጽምለት እንጂ አትጒዳው።

13 የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፣ ዋና አዛዡ ናቡሸዝባን፣ ከፍተኛ ሹሙ ኤርጌል ሳራስር እንዲሁም ሌሎች የባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ሁሉ፣

14 ልከው ኤርምያስን ከዘበኞች አደባባይ አስወጡት፤ የሳፋን ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወደ ቤቱ እንዲወስደው በዐደራ ሰጡት፤ ኤርምያስም በራሱ ሕዝብ መካከል ተቀመጠ።

15 ኤርምያስ በዘበኞች አደባባይ ታስሮ በነበረበት ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ እንዲህ ሲል መጣ፤

16 “ሂድና ለኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ እንዲህ በለው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እድገት ሳይሆን ጥፋት በማምጣት በዚህች ከተማ ላይ ቃሌን እፈጽማለሁ፤ በዚያ ጊዜ በዐይንህ እያየህ ይህ ይፈጸማል።

17 አንተን ግን በዚያ ቀን አድንሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ለምትፈራቸው ሰዎች ዐልፈህ አትሰጥም።