ሕዝቅኤል 32:21-27 NASV

21 በመቃብርም ውስጥ ኀያላኑ መሪዎች ስለ ግብፅና ስለ ተባባሪዎቿ፣ ‘ወደ ታች ወርደዋል፤ በሰይፍ ከተገደሉትና ካልተገረዙትም ጋር በአንድ ላይ ተጋድመዋል’ ይላሉ።

22 “አሦር ከመላው ሰራዊቷ ጋር በዚያ ትገኛለች፤ በሰይፍ በወደቁባትና በታረዱባት ሰዎች ሁሉ መቃብር ተከባለች።

23 መቃብራቸው በጥልቁ ጒድጓድ ውስጥ ነው፤ ሰራዊቷም በመቃብሯ ዙሪያ ተረፍርፏል። በሕያዋን ምድር ሽብርን የነዙ ሁሉ ታርደዋል፤ በሰይፍም ወድቀዋል።

24 “ኤላም በዚያ አለች፤ ሰራዊቷም ሁሉ በመቃብሯ ዙሪያ አለ፤ ሁሉም ታርደዋል፤ በሰይፍ ወድቀዋል። በሕያዋን ምድር ሽብር የነዙ ሁሉ ሳይገረዙ ከምድር በታች ወርደዋል፤ ወደ ጒድጓድ ከወረዱት ጋር ዕፍረታቸውን ተሸክመዋል፤

25 በመቃብሯ ዙሪያ ካለው መላው ሰራዊቷ ጋር፣ በታረዱት መካከል መኝታ ተዘጋጅቶላታል። ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ ሽብራቸው በሕያዋን ምድር ስለ ተነዛ፣ ወደ ጒድጓድ ከሚወርዱት ጋር ዕፍረታቸውን ይሸከማሉ፤ በታረዱትም መካከል ይጋደማሉ።

26 “ሞሳህና ቶቤል መቃብሮቻቸው በብዙ ሰራዊታቸው መቃብር ተከበው ይገኛሉ፤ ሁሉም ያልተገረዙ ሲሆኑ፣ በሕያዋን ምድር ሽብራቸውን ስለነዙ በሰይፍ ተገድለዋል።

27 ከዘመናት በፊት ከወደቁት ከኀያላን ሰዎች፣ ከእነዚያ ሰይፋቸውን ተንተርሰው፣ ጋሻቸውንም ደረታቸው ላይ ይዘው ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ መቃብር ከወረዱት ጋር አይጋደሙምን? የእነዚህ ተዋጊዎች ሽብር በሕያዋን ምድር ባሉት ኀያላን ላይ ቢደርስም የኀጢአታቸው ቅጣት በዐጥንታቸው ላይ ይሆናል።