ኤርምያስ 35:5-11 NASV

5 በሬካባውያንም ሰዎች ፊት በወይን ጠጅ የተሞሉ ማድጋዎችን አቀረብሁ፤ ዋንጫዎችንም ሰጥቻቸው፣ “በሉ፤ የወይን ጠጅ ጠጡ” አልኋቸው።

6 እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፤ “የወይን ጠጅ አንጠጣም፤ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እንዲህ ብሎ አዝዞናል፤ ‘እናንተና ዘራችሁ ከቶ የወይን ጠጅ አትጠጡ፤

7 ቤት አትሥሩ፤ ዘር አትዝሩ፤ ወይን አትትከሉ፤ ሁል ጊዜ በድንኳን ኑሩ እንጂ ከእነዚህ ነገሮች አንዱም አይኑራችሁ፤ ይህም ሲሆን እንደ መጻተኛ በሆናችሁበት ምድር ረዥም ዘመን ትኖራላችሁ።’

8 እኛም አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ ፈጽመናል፤ እኛና ሚስቶቻችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም የወይን ጠጅ ጠጥተን አናውቅም፤

9 የምንቀመ ጥበትም ቤት አልሠራንም፤ የወይን ቦታ፣ የዕርሻ ስፍራ ወይም የእህል ዘር የለንም።

10 በድንኳን ኖረናል፤ አባታችን ኢዮናዳብ ያዘዘንንም ሁሉ ጠብቀናል።

11 ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደናፆር ይህችን ምድር በወረረ ጊዜ፣ ኑ፤ ከባቢሎን ሰራዊትና ከሶርያ ሰራዊት ሸሽተን ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ’ ተባባልን፤ ስለዚህም በኢየሩሳሌም ተቀመጥን።”