1 እግዚአብሔር ቸር ነውና አመስግኑት፤ምሕረቱም ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።
2 የእስራኤል ሕዝብ፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል።
3 የአሮን ቤት፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል።
4 እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፣“ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበሉ።
5 በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እግዚአብሔርም መለሰልኝ፤ ከመጠበብም አወጣኝ።
6 እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
7 ይረዳኝ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤የጠላቶቼንም ውድቀት አያለሁ።
8 ሰውን መከታ ከማድረግ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
9 በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
10 ሕዝቦች ሁሉ ከበቡኝ፤ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ።
11 መክበቡንስ በየአቅጣጫው ከበቡኝ፤ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ።
12 እንደ ንብ መንጋ ከበቡኝ፤ነገር ግን እንደሚነድ እሾኽ ከሰሙ፤በእርግጥም በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ።
13 ተገፍትሬ ልወድቅ ተንገደገድሁ፤ እግዚአብሔር ግን ረዳኝ።
14 እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤አዳኝ ሆነልኝ።
15 በጻድቃን ድንኳን የእልልታና የሆታ ድምፅ፣እንዲህ እያለ ያስተጋባል፤“የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች፤
16 የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አለች፤ የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች።
17 ተርፌ በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም፤ የእግዚአብሔርንም ሥራ ገና እናገራለሁ።
18 መገሠጹን እግዚአብሔር እጅግ ገሥጾኛል፤ነገር ግን ለሞት አሳልፎ አልሰጠኝም።
19 የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤በዚያ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
20 ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ጻድቃን በእርሷ በኩል ይገባሉ።
21 ሰምተህ መልሰህልኛልና፣አዳኝም ሆነህልኛልና አመሰግንሃለሁ።
22 ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።
23 እግዚአብሔር ይህን አደረገ፤ለዐይናችንም ድንቅ ናት።
24 እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤በእርሷ ሐሤት እናድርግ፤ ደስም ይበለን።
25 እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ አድነን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ አሳካልን።
26 በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው። ከእግዚአብሔር ቤት ባረክናችሁ።
27 እግዚአብሔር አምላክ ነው፤ብርሃኑንም በላያችን አበራ፤እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ በመውጣት፣ዝንጣፊ ይዛችሁ በዓሉን ከሚያከብሩት ጋር ተቀላቀሉ።
28 አንተ አምላኬ ነህ፤ አመሰግንሃለሁ፤አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።
29 ቸር ነውና፣ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ምሕረቱም ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።