1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጣልኸን፤ አንኰታኰትኸን፤ተቈጣኸንም፤ አሁን ግን መልሰህ አብጀን።
2 ምድሪቱን አናወጥሃት፤ ፍርክስክስ አደረግሃት፤ትንገዳገዳለችና ስብራቷን ጠግን።
3 ለሕዝብህ አበሳውን አሳየኸው፤ናላ የሚያዞር የወይን ጠጅ እንድንጠጣም ሰጠኸን።
4 ነገር ግን ከቀስት እንዲያመልጡ፣ለሚፈሩህ ምልክት አቆምህላቸው። ሴላ
5 ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፣በቀኝ እጅህ ርዳን፤ መልስም ስጠን።
6 እግዚአብሔር ከመቅደሱ እንዲህ ሲል ተናገረ፤“ደስ እያለኝ የሴኬምን ምድር እሸነሽናለሁ፤የሱኮትን ሸለቆ አከፋፍላለሁ።
7 ገለዓድ የእኔ ነው፤ ምናሴም የእኔ ነው፤ኤፍሬም የራስ ቍሬ ነው፤ይሁዳም በትረ መንግሥቴ ነው።
8 ሞዓብ የመታጠቢያ ገንዳዬ ነው፤በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እወረውራለሁ፤በፍልስጥኤም ላይ በድል እልል እላለሁ።”
9 ወደ ተመሸገው ከተማ ማን ያመጣኛል?ማንስ ወደ ኤዶምያስ ይመራኛል?
10 አምላክ ሆይ፤ የጣልኸን አንተ አይደለህምን?እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰራዊታችን ጋር እኮ አልወጣ አልህ!
11 በጠላት ላይ ድልን አቀዳጀን፤የሰው ርዳታ ከንቱ ነውና።
12 በእግዚአብሔር ክንደ ብርቱ እንሆናለን፤ጠላቶቻችንን የሚረጋግጥልን እርሱ ነውና።