መዝሙር 58 NASV

የምድር ዳኞች ፈራጅ

ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዘመር፤ የዳዊት ቅኔ

1 ኀያላን ሆይ፤ በውኑ ጽድቅ ከአፋችሁ ይወጣል?የሰው ልጆች ሆይ፤ በቅን ትፈርዳላችሁን?

2 የለም፤ በልባችሁ ክፋትን ታውጠነጥናላችሁ፤በእጃችሁም ዐመፅን በምድር ላይ ትጐነጒናላችሁ።

3 ክፉዎች በማሕፀን ሳሉ ከመንገድ የወጡ ናቸው፤ሲወለዱ ጀምሮ የተሳሳቱና ውሸታሞች ናቸው።

4 መርዛቸው እንደ እባብ መርዝ ነው፤አልሰማ ብላ ጆሮዋን እንደ ደፈነች እፉኝት ናቸው፤

5 ጆሮዋንም የደፈነችው የመተተኛውንወይም የጠቢቡን ደጋሚ ቃል ላለመስማት ነው።

6 አምላክ ሆይ፤ ጥርሳቸውን በአፋቸው ውስጥ ስበር፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንበሶቹን መንጋጋ አወላልቅ!

7 ፈጥኖ እንደሚያልፍ ወራጅ ውሃ ይጥፉ፤ቀስታቸውን ሲስቡ ፍላጻቸው ዱልዱም ይሁን።

8 ሲሄድ እንደሚቀልጥ ቀንድ አውጣ ይሁኑ፤ፀሓይን እንደማያይ ጭንጋፍ ይሁኑ።

9 የእሾኽ እሳት ገና ድስታችሁን ሳያሰማው፣እርጥቡንም ደረቁንም እኩል በዐውሎ ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል።

10 ጻድቃን በቀልን ባዩ ጊዜ ደስ ይላቸዋል፤እግራቸውንም በግፈኞች ደም ይታጠባሉ።

11 ሰዎችም፣ “በእርግጥ ለጻድቃን ብድራት ተቀምጦላቸዋል፤በእውነትም በምድር ላይ የሚፈርድ አምላክ አለ” ይላሉ።