መዝሙር 144 NASV

የጦርነት መዝሙር

የዳዊት መዝሙር

1 እጆቼን ለጦርነት፣ ጣቶቼን ለውጊያ የሚያሠለጥን፣ እግዚአብሔር ዐለቴ ይባረክ።

2 እርሱ አፍቃሪ አምላኬና ጽኑ ዐምባዬ ነው፤ምሽጌና ታዳጊዬ፣የምከለልበትም ጋሻዬ ነው፤ሕዝቤን የሚያስገዛልኝም እርሱ ነው።

3 እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን ያህል በልብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?ታስበውስ ዘንድ የሰው ልጅ እስከዚህ ምንድን ነው?

4 ሰው እንደ እስትንፋስ ነው፤ዘመኑም ፈጥኖ እንደሚያልፍ ጥላ ነው።

5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰማያትህን ሰንጥቀህ ውረድ፤ይጤሱም ዘንድ ተራሮችን ዳስስ።

6 የመብረቅ ብልጭታ ልከህ በትናቸው፤ፍላጻህን ሰደህ ግራ አጋባቸው።

7 እጅህን ከላይ ዘርጋ፤ከኀይለኛ ውሃ፣ከባዕዳንም እጅ፣ታደገኝ፤ አድነኝም፤

8 አንደበታቸው ሐሰትን ይናገራል፤ቀኝ እጃቸውም የቅጥፈት ቀኝ እጅ ናት።

9 አምላክ ሆይ፤ አዲስ ቅኔ እቀኝልሃለሁ፤ዐሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልሃለሁ።

10 ነገሥታትን ድል የሚያጐናጽፍ፣ባሪያውን ዳዊትን ከሚጐዳ ሰይፍ የሚያድነው እርሱ ነው።

11 አንደበታቸው ሐሰትን ከሚናገር፣ቀኝ እጃቸው የቅጥፈት ቀኝ እጅ ከሆነችው፣ከባዕዳን እጅ፣ታደገኝ፤ አድነኝም።

12 ወንዶች ልጆቻችን በወጣትነታቸው፣የተሟላ ዕድገት እንዳገኘ ተክል፣ሴቶች ልጆቻችንም ቤተ መንግሥት ለማስጌጥ፣እንደ ተቀረጹ የማእዘን ዐምዶች ይሁኑ።

13 ጐተራዎቻችን በተለያየ የእህል ዐይነት፣የተሞሉ ይሁኑ፤በጎቻችን እስከ ሺህ ይውለዱ፤በመስኮቻችንም እስከ ዐሥር ሺህ ይባዙ።

14 ከብቶቻችን ይክበዱ፤አይጨንግፉ፤ አይጥፉም።እኛም በምርኮ አንወሰድ፤በአደባባዮቻችንም ዋይታ አይሰማ።

15 ይህ ባርኮት ገንዘቡ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው።