መዝሙር 146 NASV

ለረድኤት አምላክ ምስጋና

1 ሃሌ ሉያ።ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ።

2 በምኖርበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርንአመሰግናለሁ፤በሕይወትም እስካለሁ ለአምላኬ እዘምራለሁ።

3 በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ።

4 መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።

5 ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው ምስጉን ነው፤

6 እርሱ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣በእነዚህም ውስጥ ያለውን ሁሉ የፈጠረ፣ታማኝነቱንም ለዘላለም የሚጠብቅ ነው፤

7 ለተበደሉት የሚፈርድ፣ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ እርሱ ነው፤ እግዚአብሔር እስረኞችን ከእስራት ያወጣል፤

8 እግዚአብሔር የዕዉራንን ዐይን ያበራል፤ እግዚአብሔር የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወዳል፤

9 እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ድኻ ዐደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል።

10 እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽ ለትውልድ ሁሉ ንጉሥ ነው።ሃሌ ሉያ።