መዝሙር 52 NASV

የክፉዎች ዕጣ ፈንታ

ለመዘምራን አለቃ፤ ኤዶማዊው ዶይቅ ወደ ሳኦል መጥቶ፣ “ዳዊት ወደ አቢሜሌክ ቤት መጥቶአል” ብሎ በነገረው ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት

1 ኀያል ሆይ፤ በክፋት ለምን ትኵራራለህ?አንተ በእግዚአብሔር ዐይን የተናቅህ፣እንዴትስ ዘወትር ትታበያለህ?

2 አንተ ማታለልን ሥራዬ ብለህ የያዝህ፤አንደበትህ እንደ ሰላ ምላጭ፣ጥፋትን ያውጠነጥናል።

3 ከበጎ ነገር ይልቅ ክፋትን፣እውነትን ከመናገር ይልቅ ሐሰትን ወደድህ። ሴላ

4 አንተ አታላይ አንደበት ሆይ፤ጐጂ ቃላትን ሁሉ ወደድህ!

5 እግዚአብሔር ግን ለዘላለምያንኰታኵትሃል፤ይነጥቅሃል፤ ከድንኳንህም መንጥቆ ያወጣሃል፤ከሕያዋንም ምድር ይነቅልሃል። ሴላ

6 ጻድቃን ይህን ዐይተው ይፈራሉ፤እንዲህ እያሉም ይሥቁበታል፤

7 “እግዚአብሔርን መጠጊያ ያላደረገ፣ነገር ግን በሀብቱ ብዛት የተመካ፣በክፋቱም የበረታ፣ያ ሰው እነሆ!”

8 እኔ ግን በእግዚአብሔር ቤት፣እንደለመለመ የወይራ ዛፍ ነኝ፤ከዘላለም እስከ ዘላለም፣በእግዚአብሔር ምሕረት እታመናለሁ።

9 ስላደረግኸው ነገር ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፤ስምህ መልካም ነውና ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ፤በቅዱሳንም መካከል አመሰግንሃለሁ።