መዝሙር 64 NASV

የተሳዳቢዎች ቅጣት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር

1 አምላክ ሆይ፤ የብሶት ቃሌን ስማ፤ሕይወቴንም ከሚያስፈራ የጠላት ዛቻ ከልላት።

2 ከክፉዎች አድማ ሰውረኝ፤ከዐመፀኞችም ሸንጎ ጋርደኝ።

3 እነርሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤መርዘኛ ቃላቸውንም እንደ ፍላጻ ያነጣጥራሉ።

4 አሸምቀው ንጹሑን ሰው ይነድፉታል፤ድንገት ይነድፉታል፤ አይፈሩምም።

5 ክፉ ተግባር ለማከናወን እርስ በርስ ይመካከራሉ፤በስውር ወጥመድ ለመዘርጋት ይነጋገራሉ፤“ማንስ ሊያየን ይችላል?” ይባባላሉ።

6 ግፍን ያውጠነጥናሉ፤ደግሞም፣ “የረቀቀች ሤራ አዘጋጅተናል” ይላሉ፤አቤት! ልቡ፣ አእምሮውም እንዴት ጥልቅ ነው!

7 እግዚአብሔር ግን በፍላጻው ይነድፋቸዋል፤እነርሱም ድንገት ይቈስላሉ።

8 በገዛ ምላሳቸው ያሰናክላቸዋል፤ጥፋትንም ያመጣባቸዋል፤የሚያዩአቸውም ሁሉ በትዝብት ራሳቸውን ይነቀንቃሉ።

9 የሰው ልጆች ሁሉ ይፈራሉ፤የእግዚአብሔርን ሥራ በይፋ ያወራሉ፤ያደረገውንም በጥሞና ያሰላስላሉ።

10 ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይበለው፤እርሱንም መጠጊያ ያድርገው፤ልበ ቅኖችም ሁሉ ደስ ይበላቸው።