መዝሙር 74 NASV

ስለ መቅደሱ መፍረስ የቀረበ ጸሎት

የአሳፍ ትምህርት

1 አምላክ ሆይ፤ ለዘላለም የጣልኸን ለምንድን ነው?በማሰማሪያህ ባሉ በጎችህስ ላይ ቍጣህ ለምን ነደደ?

2 ጥንት ገንዘብህ ያደረግሃትን ጉባኤ፣የዋጀሃትን የርስትህን ነገድ፣መኖሪያህ ያደረግሃትን የጽዮን ተራራ አስብ።

3 እርምጃህን ለዘላለሙ ባድማ ወደ ሆነው አቅና፤ጠላት በመቅደስህ ውስጥ ያለውን ሁሉ አበላሽቶአል።

4 ጠላቶችህ በመገናኛ ስፍራህ መካከል ደነፉ፤አርማቸውንም ምልክት አድርገው በዚያ አቆሙ።

5 በጫካ መካከል ዛፎችን ለመቍረጥ፣መጥረቢያ የሚያነሣ ሰው መሰሉ።

6 በእደ ጥበብ ያጌጠውን ሥራ ሁሉ፣በመጥረቢያና በመዶሻ ሰባበሩት።

7 መቅደስህን አቃጥለው አወደሙት፤የስምህንም ማደሪያ አረከሱ።

8 በልባቸውም፣ “ፈጽሞ እንጨቍናቸዋለን” አሉ፤እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ የተመለከበትን ስፍራ ሁሉ አቃጠሉ።

9 የምናየው ምልክት የለም፤ከእንግዲህ የሚነሣ አንድም ነቢይ የለም፤ይህ እስከ መቼ እንደሚቀጥል የሚያውቅ በእኛ ዘንድ የለም።

10 አምላክ ሆይ፤ ጠላት የሚያሾፈው እስከ መቼ ነው?ባላንጣስ ለዘላለም በስምህ ያላግጣልን?

11 እጅህን ለምን ትሰበስባለህ?ቀኝ እጅህን ለምን በብብትህ ሥር ታቆያለህ?

12 አምላክ ሆይ፤ አንተ ከጥንት ጀምሮ ንጉሤ ነህ፤በምድር ላይ ማዳንን አደረግህ።

13 ባሕርን በኀይልህ የከፈልህ አንተ ነህ፤የባሕሩንም አውሬ ራሶች በውሃ ውስጥ ቀጠቀጥህ።

14 የሌዋታንን ራሶች አደቀቅህ፤ለምድረ በዳ ፍጥረታትም ምግብ አድርገህ የሰጠሃቸው፣

15 ምንጮችንና ፈሳሾችን ያፈለቅህ አንተ ነህ፤ሳያቋርጡ የሚፈሱትንም ወንዞች አደረቅህ።

16 ቀኑ የአንተ ነው፤ ሌሊቱም የአንተ ነው፤ጨረቃንና ፀሓይን አንተ አጸናሃቸው።

17 የምድርን ዳርቻ ሁሉ የወሰንህ አንተ ነህ፤በጋውንም ክረምቱንም አንተ ሠራህ።

18 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላት እንዴት እንደሚያሾፍ፣ከንቱ ሕዝብም ስምህን እንዴት እንዳቃለለ አስብ።

19 የርግብህን ነፍስ አሳልፈህ ለዱር አራዊት አትስጥ፤የችግረኞች ሕዝብህን ሕይወት ለዘላለሙ አትርሳ።

20 ኪዳንህን አስብ፤የዐመፅ መናኸሪያ በምድሪቱ ጨለማ ስፍራዎች ሞልተዋልና።

21 የተጨቈኑት አፍረው አይመለሱ፤ድኾችና ችግረኞች ስምህን ያመስግኑ።

22 አምላክ ሆይ፤ ተነሥ፤ ለዐላማህ ተሟገት፤ከንቱ ሰው ቀኑን ሙሉ እንደሚያላግጥብህ አስብ።

23 የባላጋራዎችህን ድንፋታ፣ዘወትር የሚነሣውን የጠላቶችህን ፉከራ አትርሳ።