1 እግዚአብሔር ይነሣ፤ ጠላቶቹ ይበተኑ፤የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ።
2 ጢስ እንደሚበንን፣እንዲሁ አብንናቸው።ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፣ክፉዎችም እንዲሁ ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ።
3 ጻድቃን ግን ደስ ይበላቸው፤በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት ያድርጉ፤ደስታንና ፍስሓን የተሞሉ ይሁኑ።
4 ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ለስሙም ተቀኙ፤በደመናት ላይ የሚሄደውን ከፍ አድርጉት፤ስሙ እግዚአብሔር በተባለው ፊት፣እጅግ ደስ ይበላችሁ።
5 እግዚአብሔር በተቀደሰ ማደሪያው፣ለድኻ አደጉ አባት፣ ለባልቴቲቱም ተሟጋች ነው።
6 እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤተ ሰብ መካከል ያኖራል፤እስረኞችን ነጻ አውጥቶ ያስፈነድቃል፤ዐመፀኞች ግን ምድረ በዳ ይኖራሉ።
7 እግዚአብሔር ሆይ፤ በሕዝብህ ፊት በወጣህ ጊዜ፣በምድረ በዳም በተጓዝህ ጊዜ፣ ሴላ
8 በሲና አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣በእስራኤል አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣ምድር ተንቀጠቀጠች፤ሰማያትም ዶፍ አወረዱ።
9 እግዚአብሔር ሆይ፣ በቂ ዝናብ አዘነብህ፤ክው ብሎ የደረቀውን ርስትህን አረሰረስህ።
10 መንጋህ መኖሪያው አደረጋት፤እግዚአብሔር ሆይ፤ ከበረከትህ ለድኾች ሰጠህ።
11 ጌታ እንዲህ ሲል ቃሉን አስተላለፈ፤ትእዛዙን የሚያውጁትም ብዙ ሰራዊት ናቸው፤
12 “የሰራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፤በሰፈር የዋሉ ሴቶችም ምርኮን ተካፈሉ።
13 በበጎች በረት መካከል ብትገኙ እንኳ፣ከብር እንደ ተሠሩ የርግብ ክንፎች፣በቅጠልያ ወርቅ እንደ ተለበጡ ላባዎች ናችሁ።”
14 ሁሉን ቻዩ በዚያ የነበሩትን ነገሥታት በበተነ ጊዜ፣በሰልሞን እንደሚወርድ በረዶ አደረጋቸው።
15 አንተ ብርቱ ተራራ፣ የባሳን ተራራ ሆይ፤አንተ ባለ ብዙ ጫፍ ተራራ፣ የባሳን ተራራ፤
16 እናንተ ባለ ብዙ ጫፍ ተራሮች ሆይ፤እግዚአብሔር ሊኖርበት የመረጠውን ተራራ፣በእርግጥ እግዚአብሔር ለዘላለም የሚኖርበትን ተራራ ለምን በምቀኝነት ዐይን ታያላችሁ?
17 የእግዚአብሔር ሠረገላዎች እልፍ አእላፍ ናቸው፤ሺህ ጊዜም ሺህ ናቸው፤ጌታ ከሲና ወደ መቅደሱ ገባ።
18 ወደ ላይ ዐረግህ፤ምርኮ አጋበስህ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ አንተ በዚያ ትኖር ዘንድ፣ከዐመፀኞችም ሳይቀር፣ከሰዎች ስጦታን ተቀበልህ።
19 ሸክማችንን በየዕለቱ የሚሸከምልን፣አዳኝ አምላካችን፣ ጌታ ይባረክ። ሴላ
20 አምላካችን የሚያድን አምላክ ነው፤ከሞት ማምለጥ የሚቻለውም በጌታ በእግዚአብሔር ነው።
21 በእርግጥ እግዚአብሔር የጠላቶቹን ራስ፣በኀጢአታቸውም የሚጸኑትን ሰዎች ጠጒራም አናት ይፈነካክታል።
22 ጌታ እንዲህ ይላል፤ “ከባሳን መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ከባሕርም ጥልቀት አውጥቼ አመጣቸዋለሁ፤
23 እግርህ በጠላትህ ደም ውስጥ እንዲጠልቅ፣የውሻህም ምላስ ከጠላትህ ድርሻውን እንዲያገኝ ነው።”
24 አምላክ ሆይ፤ የክብር አካሄድህ ታየ፤ይህም አምላኬና ንጉሤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያደርገው የክብር አካሄድ ነው።
25 መዘምራን ከፊት፣ መሣሪያ የሚጫወቱ ከኋላ ሆነው ሲሄዱ፣ከበሮ የሚመቱ ቈነጃጅትም በመካከላቸው ነበሩ።
26 እግዚአብሔርን በጉባኤ አመስግኑት፤ ከእስራኤል ምንጭ የተገኛችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑ።
27 የሚመራቸው ትንሹ ብንያም ነው፤በዚያ በብዙ የሚቈጠሩ የይሁዳ መሳፍንት፣እንዲሁም የዛብሎንና የንፍታሌም መሳፍንት ይገኛሉ።
28 እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀይልህን እዘዝ፤አምላክ ሆይ ቀድሞ እንዳደረግህልን አሁንም ብርታትህን አሳየን።
29 በኢየሩሳሌም ስላለው ቤተ መቅደስህ፣ነገሥታት እጅ መንሻ ያመጡልሃል።
30 በሸምበቆ መካከል ያሉትን አራዊት፣በሕዝቡ ጥጆች መካከል ያለውንም የኮርማ መንጋ ገሥጽ፤ብር ይገብር ዘንድም ይንበርከክ፤ጦርነትን የሚወዱ ሕዝቦችንም በትናቸው።
31 መኳንንት ከግብፅ ይመጣሉ፤ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።
32 የምድር መንግሥታት ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ለጌታ ተቀኙ። ሴላ
33 ከጥንት ጀምሮ ከነበሩት ሰማያት በላይ ለወጣው፣በኀያል ድምፁ ለሚያስገመግመው ዘምሩ።
34 ግርማው በእስራኤል ላይ፣ኀይሉም ከደመናት በላይ ነው፣እግዚአብሔርን ብርታት የአንተ ነው በሉት።
35 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በመቅደስህ ድንቅ ነህ፤የእስራኤል አምላክ ለሕዝቡ ኀይልና ብርታትን ይሰጣል።እግዚአብሔር ይባረክ!