1 መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው።
2 ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣በፍጹምም ልብ የሚሹት የተባረኩ ናቸው፤
3 ዐመፅን አያደርጉም፤ነገር ግን በመንገዱ ይሄዳሉ።
4 ጠንቅቀን እንጠብቃት ዘንድ፣አንተ ሥርዐትን አዘሃል።
5 ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ፣ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ ኖሮ!
6 ወደ ትእዛዛትህ ስመለከት፣በዚያን ጊዜ አላፍርም።
7 የጽድቅ ፍርድህን ስማር፣በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ።
8 ሥርዐትህን እጠብቃለሁ፤ፈጽመህ አትተወኝ።
9 ጒልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል?በቃልህ መሠረት በመኖር ነው።
10 በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ከትእዛዛትህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ።
11 አንተን እንዳልበድል፣ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።
12 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ሥርዐትህን አስተምረኝ።
13 ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣በከንፈሬ እናገራለሁ።
14 ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል።
15 ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ።
16 በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ቃልህንም አልዘነጋም።
17 ሕያው እንድሆን፣ ቃልህንም እንድጠብቅ፣ለአገልጋይህ መልካም አድርግ።
18 ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ዐይኖቼን ክፈት።
19 እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር።
20 ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣ነፍሴ እጅግ ዛለች።
21 ከትእዛዛትህ የሳቱትን፣እብሪተኞችንና ርጉሞችን ትገሥጻለህ።
22 ምስክርነትህን ጠብቄአለሁና፣ስድብንና ንቀትን ከእኔ አርቅ።
23 ገዦች ተቀምጠው ቢዶልቱብኝ እንኳ፣አገልጋይህ ሥርዐትህን ያሰላስላል።
24 ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው፤መካሪዬም ነው።
25 ነፍሴ ከዐፈር ተጣበቀች፤እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።
26 ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ፤ አንተም መለስህልኝ፤ሥርዐትህን አስተምረኝ።
27 የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፤እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ።
28 ነፍሴ በሐዘን ተዝለፈለፈች፤እንደ ቃልህ አበርታኝ።
29 የሽንገላን መንገድ ከእኔ አርቅ፤ሕግህን በጸጋህ ስጠኝ።
30 የእውነትን መንገድ መርጫለሁ፤ሕግህንም ፊት ለፊቴ አድርጌአለሁ።
31 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከምስክርነትህ ጋር ተጣብቄአለሁ፤አሳልፈህ ለውርደት አትስጠኝ።
32 ልቤን አስፍተህልኛልና፣በትእዛዛትህ መንገድ እሮጣለሁ።
33 እግዚአብሔር ሆይ፤ የሥርዐትህን መንገድ አስተምረኝ፤እኔም እስከ መጨረሻው እጠብቀዋለሁ።
34 ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው፣ ማስተዋልን ስጠኝ።
35 በእርሷ ደስ ይለኛልና፣በትእዛዝህ መንገድ ምራኝ።
36 ከራስ ጥቅም ይልቅ፣ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል።
37 ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ፤በራስህ መንገድ እንደ ገና ሕያው አድርገኝ።
38 ትፈራ ዘንድ፣ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ፈጽም።
39 የምፈራውን መዋረድ ከእኔ አርቅ፤ደንብህ መልካም ነውና።
40 እነሆ፤ ድንጋጌህን ናፈቅሁ፤በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ።
41 እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ወደ እኔ ይምጣ፤ማዳንህም እንደ ቃልህ ይላክልኝ።
42 በቃልህ ታምኛለሁና፣ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ።
43 ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ።
44 ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ።
45 ሥርዐትህን እሻለሁና፣እንደ ልቤ ወዲያ ወዲህ እመላለሳለሁ።
46 ምስክርነትህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ይህን በማድረግም ዕፍረት አይሰማኝም።
47 እኔ እወደዋለሁና፣በትእዛዝህ ደስ ይለኛል።
48 እጆቼን ወደምወዳቸው ትእዛዛትህ አነሣለሁ፤ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ።
49 ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና።
50 ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት።
51 እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም።
52 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን ዐሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ።
53 ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣ቍጣ ወረረኝ።
54 በእንግድነቴ አገር፣ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት።
55 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤ሕግህንም እጠብቃለሁ።
56 ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ይህችም ተግባሬ ሆነች።
57 እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ።
58 በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ።
59 መንገዴን ቃኘሁ፤አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ።
60 ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም።
61 የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም።
62 ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ።
63 እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣ሥርዐትህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ።
64 እግዚአብሔር ሆይ፤ ምድር በምሕረትህ ተሞላች፤ሥርዐትህን አስተምረኝ።
65 እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ፣ለአገልጋይህ በጎ ውለሃል።
66 በትእዛዛትህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትንአስተምረኝ።
67 እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ።
68 አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገው መልካም ነው፤እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ።
69 እብሪተኞች ስሜን በሐሰት አጠፉ፤እኔ ግን ትእዛዝህን በፍጹም ልብ እጠብቃለሁ።
70 ልባቸው የሠባና የደነደነ ነው፤እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል።
71 ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ።
72 ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል።
73 እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ትእዛዛትህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ።
74 ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው።
75 እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደሆነ ዐወቅሁ።
76 ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ።
77 ሕግህ ደስታዬ ነውና፣በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ።
78 እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤እኔ ግን ትእዛዛትህን አሰላስላለሁ።
79 አንተን የሚፈሩህ፣ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ።
80 እኔ እንዳላፍር፤ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን።
81 ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።
82 “መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።
83 ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣ሥርዐትህን አልረሳሁም።
84 የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው?ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን?
85 በሕግህ መሠረት የማይሄዱ፣እብሪተኞች ማጥመጃ ጒድጓድ ቈፈሩልኝ።
86 ትእዛዛትህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤ሰዎች ያለ ምክንያት አሳደውኛልና ርዳኝ።
87 ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም።
88 እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ።
89 እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
90 ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች።
91 ሁሉም አገልጋይህ ነውና፣በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ።
92 ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር።
93 በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም።
94 እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤ሕግህንም ፈልጌአለሁና።
95 ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል፤እኔ ግን ምስክርነትህን አሰላስላለሁ።
96 ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ እንዳለው አየሁ፤ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።
97 አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።
98 ትእዛዛትህ ምንጊዜም ስለማይለዩኝ፣ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ።
99 ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ።
100 መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ።
101 ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ።
102 አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም።
103 ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው!ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው።
104 ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።
105 ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ለመንገዴም ብርሃን ነው።
106 የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ።
107 እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።
108 እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቅጄ ያቀረብሁትን የአፌን የምስጋና መሥዋዕት ተቀበል፤ሕግህንም አስተምረኝ።
109 ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ሕግህን ግን አልረሳሁም።
110 ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤እኔ ግን መመሪያህን አልተላለፍሁም።
111 ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና።
112 ትእዛዝህን ለዘላለም፣ እስከ ወዲያኛው ለመፈጸም፣ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ።
113 መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤ሕግህን ግን ወደድሁ።
114 አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ።
115 የአምላኬን ትእዛዛት እጠብቅ ዘንድ፣እናንት ክፉ አድራጊዎች፣ ከእኔ ራቁ።
116 እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር።
117 ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ።
118 መሰሪነታቸው በከንቱ ነውና፣ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው።
119 የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ።
120 ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ፍርድህንም እፈራለሁ።
121 ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ።
122 ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤እብሪተኛ እንዲጨቍነኝ አትፍቀድላቸው።
123 ዐይኖቼ ማዳንህን፣የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።
124 ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ መጠን አድርግ፤ሥርዐትህንም አስተምረኝ።
125 እኔ ባሪያህ ነኝ፤ምስክርነትህን ዐውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።
126 እግዚአብሔር ሆይ፤ሕግህ እየተጣሰ ነውና፣ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው።
127 ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣ትእዛዛትህን ወደድሁ።
128 መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ፤ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።
129 ምስክርነትህ ሁሉ ድንቅ ነው፤ስለዚህ ነፍሴ ትጠብቀዋለች።
130 የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል።
131 ትእዛዝህን ናፍቄአለሁና፣አፌን ከፈትሁ፤ አለከለክሁም።
132 ስምህን ለሚወዱ ማድረግ ልማድህ እንደሆነ ሁሉ፣ወደ እኔ ተመልሰህ፣ ምሕረት አድርግልኝ።
133 አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ።
134 ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል፣ከሰዎች ጥቃት ታደገኝ።
135 በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፤ሥርዐትህንም አስተምረኝ።
136 ሕግህ ባለመከበሩ፤እንባዬ እንደ ውሃ ይፈሳል።
137 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ፍርድህም ትክክል ነው።
138 ምስክርነትህን በጽድቅ አዘዝህ፤እጅግ አስተማማኝም ነው።
139 ጠላቶቼ ቃልህን ዘንግተዋልና፣ቅናት አሳረረኝ።
140 ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፤ባሪያህም ወደደው።
141 እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ነገር ግን መመሪያህን አልዘነጋሁም።
142 ጽድቅህ ዘላለማዊ ጽድቅ ነው፤ሕግህም እውነት ነው።
143 መከራና ሥቃይ ደርሶብኛል፤ነገር ግን ትእዛዝህ ደስታዬ ነው።
144 ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።
145 እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ፤ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ።
146 ወደ አንተ እጣራለሁና አድነኝ፤ምስክርነትህንም እጠብቃለሁ።
147 ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድ ተነሥቼ እጮኻለሁ፤ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።
148 ቃልህን አሰላስል ዘንድ፣ዐይኔ ሌሊቱን ሙሉ ሳይከደን ያድራል።
149 እንደ ቸርነትህ መጠን ድምፄን ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ሕግህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።
150 ደባ የሚያውጠነጥኑ ወደ እኔ ቀርበዋል፤ከሕግህ ግን የራቁ ናቸው።
151 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ቅርብ ነህ፤ትእዛዛትህም ሁሉ እውነት ናቸው።
152 ለዘላለም እንደ መሠረትሃቸው፣ከጥንት ምስክርነትህ ተረድቻለሁ።
153 ሕግህን አልረሳሁምና፣ ሥቃዬን ተመልከት፤ ታደገኝም።
154 ተሟገትልኝ፤ አድነኝም፤እንደ ቃልህም ሕያው አድርገኝ።
155 ሥርዐትህን ስለማይሹ፣ድነት ከክፉዎች የራቀ ነው።
156 እግዚአብሔር ሆይ፤ ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤እንደ ሕግህ ሕያው አድርገኝ።
157 የሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ ብዙዎች ናቸው፤እኔ ግን ከምስክርህ ዘወር አላልሁም።
158 ቃልህን አይጠብቁምና፣ከዳተኞችን አይቼ አርቃቸዋለሁ።
159 መመሪያህን እንዴት እንደምወድ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ።
160 ቃልህ በሙሉ እውነት ነው፤ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው።
161 ገዦች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ፤ልቤ ግን ከቃልህ የተነሣ እጅግ ፈራ።
162 ትልቅ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፤በቃልህ ደስ አለኝ።
163 ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁ፤ሕግህን ግን ወደድሁ።
164 ጻድቅ ስለ ሆነው ሕግህ፤በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ።
165 ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ዕንቅፋትም የለባቸውም።
166 እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ትእዛዝህንም እፈጽማለሁ።
167 ነፍሴ ምስክርነትህን ትጠብቃለች፤እጅግ እወደዋለሁና።
168 መንገዴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነውና፣ሕግህንና ምስክርነትህን እጠብቃለሁ።
169 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴ ከፊትህ ይድረስ፤እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ።
170 ልመናዬ ከፊትህ ይድረስ፤እንደ ቃልህም ታደገኝ።
171 ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና፣ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ።
172 ትእዛዛትህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዛት ናቸውና፣አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር።
173 ትእዛዝህን መርጫለሁና፣እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን።
174 እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ሕግህም ደስታዬ ነው።
175 አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤ሕግህም ይርዳኝ።
176 እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ትእዛዛትህን አልረሳሁምና፣ባሪያህን ፈልገው።