መዝሙር

ምዕራፎች 73

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ሦስተኛ መጽሐፍ

የፍትሕ አሸናፊነት

የአሳፍ መዝሙር

1እግዚአብሔር ልባቸው ንጹሕ ለሆነ፣ለእስራኤል እንዴት ቸር ነው! 2እኔ ግን እግሬ ሊሰናከል፣አዳልጦኝም ልወድቅ ጥቂት ቀረኝ። 3ክፉዎች ሲሳካላቸው አይቼ፣በዐመፀኞች ቀንቼ ነበርና። 4አንዳች ጣር የለባቸውም፤ሰውነታቸውም ጤናማና የተደላደለ ነው። 5በሰዎች የሚደርሰው ጣጣ አይደርስባቸውም፤እንደ ማንኛውም ሰው መከራ አያገኛቸውም። 6ስለዚህ ትዕቢት የዐንገት ጌጣቸው ነው፤ዐመፅንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈዋል። 7የሰባ ዐይናቸው ይጒረጠረጣል፤ልባቸውም በከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይፈስሳል። 8በፌዝና በክፋት ይናገራሉ፤ቀና ቀና ብለውም በዐመፅ ይዝታሉ። 9አፋቸውን በሰማይ ላይ ያላቅቃሉ፤አንደበታቸውም ምድርን ያካልላል። 10ስለዚህ ሕዝቡ ወደ እነርሱ ይነጒዳል፤ውሃቸውንም በገፍ ይጠጣሉ። 11“ለመሆኑ እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል?በልዑልስ ዘንድ ዕውቀት አለ?” ይላሉ። 12እንግዲህ፣ ክፉዎች ይህን ይመስላሉ፤ሁል ጊዜ ግድ የለሽና ሀብት በሀብት ናቸው። 13ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት በከንቱ ነው፤እጄንም በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሮአል! 14ቀኑን ሙሉ ተቀሠፍሁ፤ጠዋት ጠዋትም ተቀጣሁ። 15“እኔ እንደዚህ እናገራለሁ” ብልማ ኖሮ፣የልጆችህን ትውልድ በከዳሁ ነበር። 16ይህን ነገር ለመረዳት በሞከርሁ ጊዜ፣አድካሚ ተግባር መስሎ ታየኝ። 17ይኸውም ወደ አምላክ መቅደስ እስክገባ፣መጨረሻቸውንም እስካይ ድረስ ነበር። 18በእርግጥ በሚያዳልጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፤ወደ ጥፋትም አወረድሃቸው። 19እንዴት ፈጥነው በቅጽበት ጠፉ!በድንጋጤ ፈጽመው ወደሙ። 20ሰው ከሕልሙ ሲነቃ እንደሚሆነው፣ጌታ ሆይ፤ አንተም በምትነሣበት ጊዜ፣እንደ ቅዠት ከንቱ ታደርጋቸዋለህ። 21ነፍሴ በተማረረች ጊዜ፣ልቤም በተቀሠፈ ጊዜ፣ 22ስሜት የሌለውና አላዋቂ ሆንሁ፤በፊትህም እንደ እንስሳ ሆንሁ። 23ይህም ሆኖ ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፤አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል። 24በምክርህ መራኸኝ፤ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ። 25በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ?በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም። 26ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው። 27እነሆ፤ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና፤አንተ ታማኞች ያልሆኑልህን ሁሉ ታጠፋቸዋለህ። 28ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ጌታ እግዚአብሔርን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ፤ስለ ሥራህም ሁሉ እናገር ዘንድ።