መዝሙር 139 NASV

ሁሉን ዐዋቂ አምላክ

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ደግሞም ዐወቅኸኝ።

2 አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ።

3 መሄድ መተኛቴን አጥርተህ ታውቃለህ፤መንገዶቼንም ሁሉ ተረድተሃቸዋል።

4 እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ።

5 አንተ ከኋላም ከፊትም ዙሪያዬን ከለልኸኝ፤እጅህንም በላዬ አደረግህ።

6 እንዲህ ያለው ዕውቀት ለኔ ድንቅ ነው፤ልደርስበትም የማልችል ከፍ ያለ ነው።

7 ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ?ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ?

8 ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤መኝታዬንም በሲኦል ባደርግ በዚያ ትገኛለህ።

9 በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበር፣እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣

10 በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች፤ቀኝ እጅህም አጥብቃ ትይዘኛለች።

11 እኔም፣ “ጨለማው በርግጥ ይሰውረኛል፤በዙሪያዬ ያለውም ብርሃን ሌሊት ይሆናል” ብል፣

12 ጨለማ የአንተን ዐይን አይዝም፤ሌሊቱም እንደ ቀን ያበራል፤ጨለማም ብርሃንም ለአንተ አንድ ናቸውና።

13 አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ።

14 ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ሥራህ ድንቅ ነው፤ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።

15 እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ዐጥንቶቼ ከአንተ አልተደበቁም፤በምድር ጥልቀት ውስጥ በጥበብ በተሠራሁ ጊዜ፣

16 ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣በመጽሐፍ ተመዘገቡ።

17 አምላክ ሆይ፤ ለእኔ ያለህ ሐሳብ እንዴት ክቡር ነው!ቍጥሩስ ምንኛ ብዙ ነው!

18 ልቍጠራቸው ብል፣ከአሸዋ ይልቅ ይበዙ ነበር።ተኛሁም ነቃሁም፣ገና ከአንተው ጋር ነኝ።

19 አምላክ ሆይ፣ ክፉዎችን ብትገድላቸው ምናለበት!ደም የተጠማችሁ ሰዎች ሆይ፤ከእኔ ራቁ!

20 ስለ አንተ በክፋት ይናገራሉና፤ጠላቶችህም ስምህን በከንቱ ያነሣሉ።

21 እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚጠሉህን አልጠላምን?በአንተ ላይ የሚነሡትንስ አልጸየፍምን?

22 በፍጹም ጥላቻ ጠልቻቸዋለሁ፤ባላጋራዎቼም ሆነዋል።

23 እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤

24 የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤በዘላለምም መንገድ ምራኝ።