መዝሙር 28 NASV

ልመናና ምስጋና

የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ዐለቴ ሆይ፤ ሰምተህ እንዳልሰማ አትሁንብኝ፤አንተ ዝም ካልኸኝ፤ወደ ጒድጓድ እንደሚወርዱ እሆናለሁ።

2 ለርዳታ በጮኽሁ ጊዜ፣ወደ ቅዱስ ማደሪያህ፣እጆቼን በዘረጋሁ ጊዜ፣የልመናዬን ቃል ስማ።

3 በልባቸው ተንኰል እያለ፣ከባልንጀሮቻቸው ጋር በሰላም ከሚናገሩ፣ከክፉ አድራጊዎችና፣ከዐመፃ ሰዎች ጋር ጐትተህ አትውሰደኝ።

4 እንደ ሥራቸው፣እንደ ክፉ ተግባራቸው ክፈላቸው፤እንደ እጃቸው ሥራ ስጣቸው፤አጸፋውን መልስላቸው።

5 ለእግዚአብሔር ሥራ ግድ ስለሌላቸው፣ለእጆቹም ተግባራት ስፍራ ስላልሰጡ፣እርሱ ያፈርሳቸዋል፤መልሶም አይገነባቸውም።

6 የልመናዬን ቃል ሰምቶአልና፣ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን።

7 እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤ልቤ በእርሱ ይታመናል፤ እርሱም ዐግዞኛል፤ልቤ ሐሤት አደረገ፤በዝማሬም አመሰግነዋለሁ።

8 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ብርታታቸው ነው፤ለቀባውም የመዳን ዐምባ ነው።

9 ሕዝብህን አድን፤ ርስትህንም ባርክ፤እረኛ ሁናቸው፤ ለዘላለሙም ዐቅፈህ ያዛቸው።