መዝሙር

ምዕራፎች 29

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ለማዕበሉ ጌታ የቀረበ ውዳሴ

የዳዊት መዝሙር

1እናንተ ኀያላን፣ ለእግዚአብሔር ስጡ፤ክብርንና ብርታትን ለእግዚአብሔር ስጡ። 2ለስሙ የሚገባ ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤በቅድስናው ግርማ ለእግዚአብሔር ስገዱ። 3 የእግዚአብሔር ድምፅ በውሆች ላይ ነው፤የክብር አምላክ አንጐደጐደ፤ እግዚአብሔር በታላላቅ ውሆች ላይ አንጐደጐደ። 4 የእግዚአብሔር ድምፅ ኀያል ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅ ግርማዊ ነው። 5 የእግዚአብሔር ድምፅ ዝግባን ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የሊባኖስን ዝግባ ይሰባብራል። 6ሊባኖስን እንደ ጥጃ፣ስርዮንንም እንደ አውራሪስ ግልገል ያዘልላል። 7 የእግዚአብሔር ድምፅየእሳት ነበልባል ይረጫል። 8 የእግዚአብሔር ድምፅ ምድረ በዳውን ያናውጣል፤ የእግዚአብሔር ድምፅ የቃዴስን ምድረ በዳ ያናውጣል። 9 የእግዚአብሔር ድምፅ ወርካዎችን ይወዘውዛል፤ጫካዎችንም ይመነጥራል፤ሁሉም በእርሱ ቤተ መቅደስ ሆኖ “ይክበር!” ይላል። 10 እግዚአብሔር በጐርፍ ላይ ዙፋኑን ዘርግቶ ተቀምጦአል፤ እግዚአብሔር በንጉሥነቱ ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። 11 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ብርታትን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።