መዝሙር 148 NASV

ፍጥረተ ዓለም ሁሉ ያመስግን

1 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤በላይ በአርያም አመስግኑት።

2 መላእክቱ ሁሉ አመስግኑት፤ሰራዊቱ ሁሉ አመስግኑት፤

3 ፀሓይና ጨረቃ አመስግኑት፤የምታበሩ ከዋክብት ሁሉ አመስግኑት።

4 ሰማየ ሰማያት አመስግኑት፤ከሰማያትም በላይ ያላችሁ ውሆች አወድሱት።

5 እርሱ ስላዘዘ ተፈጥረዋልና፣ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት።

6 ከዘላለም እስከ ዘላለም አጸናቸው፤የማይሻርም ሕግ ደነገገላቸው።

7 የባሕር ውስጥ ግዙፍ ፍጥረትና ጥልቅ ውሆች ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት።

8 እሳትና በረዶ፣ ዐመዳይና ጭጋግ፣ትእዛዙንም የሚፈጽም ዐውሎ ነፋስ፣

9 ተራሮችና ኰረብቶች ሁሉ፣የፍሬ ዛፎችና ዝግቦች ሁሉ፣

10 የዱር አራዊትና የቤት እንስሳት ሁሉ፣በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና የሚበሩ ወፎችም፣

11 የምድር ነገሥታትና ሕዝቦች ሁሉ፣መሳፍንትና የምድር ገዦች ሁሉ፣

12 ወጣት ወንዶችና ደናግል፣አረጋውያንና ልጆች ያመስግኑት።

13 ስሙ ብቻውን ከፍ ያለ ነውና፣ክብሩም ከምድርና ከሰማይ በላይ ነውና፣እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ።

14 እርሱ ለሕዝቡ ቀንድን አስነሥቶአል፤ለቅዱሳኑ ሁሉ ምስጋና፣እጅግ ቅርቡ ለሆነው ሕዝቡ፣ ለእስራኤል ልጆች።ሃሌ ሉያ።