መዝሙር 22 NASV

የጻድቅ ሰው መከራና ተስፋ

ለመዘምራን አለቃ፤ በ“ንጋት አጋዘን” ዜማ የሚዜም፤ የዳዊት መዝሙር

1 አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?እኔን ከማዳን፣ከመቃተቴም ቃል ለምን ራቅህ?

2 አምላኬ ሆይ፤ በቀን ወደ አንተ አጮኻለሁ፤አንተ ግን አልመለስህልኝም፤በሌሊት እንኳ አላረፍሁም።

3 አንተ ግን ቅዱሱ ነጋሢ፤የእስራኤልም ምስጋና ነህ።

4 አባቶቻችን በአንተ ታመኑ፤ተማመኑብህ፤ አንተም ታደግሃቸው።

5 ወደ አንተ ጮኹ፤ ዳኑም፤በአንተም ታመኑ፤ አላፈሩም።

6 እኔ ግን ትል እንጂ ሰው አይደለሁም፤ሰው ያላገጠብኝ፣ ሕዝብም የናቀኝ ነኝ።

7 የሚያዩኝ ሁሉ ይሣለቁብኛል፤ራሳቸውንም እየነቀነቁ እንዲህ እያሉ ይዘልፉኛል፤

8 “በእግዚአብሔር ተማምኖአል፤እንግዲህ እርሱ ያድነው፤ደስ የተሰኘበትን፣እስቲ ይታደገው።”

9 አንተ ግን ከማሕፀን አወጣኸኝ፤በእናቴም ጡት ሳለሁ፣ መታመኛ ሆንኸኝ።

10 ከማሕፀን ስወጣም በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ከእናቴ ሆድ ጀምሮም አንተ አምላኬ ነህ።

11 መከራ እየተቃረበ ነውና፣የሚረዳኝም የለምና፣ከእኔ አትራቅ።

12 ብዙ ኰርማዎች ከበቡኝ፤ኀይለኛ የባሳን በሬዎችም ዙሪያዬን ቆሙ።

13 እንደሚነጥቅና እንደሚያገሣ አንበሳ፣አፋቸውን ከፈቱብኝ።

14 እንደ ውሃ ፈሰስሁ፤ዐጥንቶቼም ሁሉ ከመጋጠሚያቸው ወለቁ፤ልቤ እንደ ሰም ሆነ፤በውስጤም ቀለጠ።

15 ጒልበቴ እንደ ገል ደረቀ፤ምላሴ ከላንቃዬ ጋር ተጣበቀ፤ወደ ሞት ዐፈርም አወረድኸኝ።

16 ውሾች ከበቡኝ፤የክፉዎች ሸንጎ በዙሪያዬ ተሰልፎአል፤እጆቼንና እግሮቼንም ቸነከሩኝ።

17 ዐጥንቶቼን ሁሉ አንድ በአንድ መቍጠር እችላለሁ፤እነርሱም አፍጥጠው ይመለከቱኛል።

18 ልብሶቼን ተከፋፈሉ፤በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።

19 አንተ ግን፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ፤አጋዤ ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

20 ነፍሴን ከሰይፍ ታደጋት፤ውድ ሕይወቴንም ከውሾች ጡጫ አድናት።

21 ከአንበሶች አፍ አድነኝ፤ከአውራሪስ ቀንድም ታደገኝ።

22 ስምህን ለወንድሞቼ እነግራለሁ፤በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ።

23 እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩ፤አወድሱት፤እናንተ የያቆብ ዘር ሁላችሁ፤ አክብሩት፤የእስራኤልም ዘር ሁላችሁ፤ እርሱን ፍሩት።

24 እርሱ የተጨነቀውን ሰው ጭንቀት፣አልናቀም፤ ቸልም አላለምና፤ፊቱንም ከእርሱ አልሰወረም፤ነገር ግን ድረስልኝ ብሎ ሲጮኽ ሰማው።

25 በታላቅ ጉባኤ የማቀርበው ምስጋናዬ ከአንተ የመጣ ነው፤እርሱን በሚፈሩት ፊት ስእለቴን እፈጽማለሁ።

26 ምስኪኖች በልተው ይጠግባሉ፤ እግዚአብሔርን የሚሹትም ያመሰግኑታል፤ልባችሁም ለዘላለም ሕያው ይሁን!

27 የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስታውሳሉ፤ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳሉ፤የሕዝቦች ነገዶች ሁሉ፣በፊቱ ይሰግዳሉ።

28 መንግሥት የእግዚአብሔር ናትና፤ሕዝቦችንም የሚገዛ እርሱ ነው።

29 የምድር ከበርቴዎች ይበላሉ፤ይሰግዱለታልም፤ነፍሱን በሕይወት ማቆየት የማይችለው፣ ወደ ዐፈር፣ተመላሽ የሆነው ሁሉ በፊቱ ይንበረከካል።

30 የኋለኛው ትውልድ ያገለግለዋል፤ለመጪው ትውልድ ስለ ጌታ ይነገረዋል።

31 ገና ላልተወለደ ሕዝብ፣ጽድቁን ይነግራሉ፤እርሱ ይህን አድርጎአልና።