መዝሙር 99 NASV

ጻድቅና ቅዱስ አምላክ

1 እግዚአብሔር ነገሠ፤ሕዝቦች ይንቀጥቀጡ፤በኪሩቤል ላይ በዙፋን ተቀምጦአል፤ምድር ትናወጥ።

2 እግዚአብሔር በጽዮን ታላቅ ነው፤ከሕዝቦችም ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ብሎአል።

3 ታላቁንና አስፈሪውን ስምህን ይወድሱ፤እርሱ ቅዱስ ነው።

4 ፍትሕን የምትወድ፣ ኀያል ንጉሥ ሆይ፤አንተ ትክክለኝነትን መሠረትህ፤ፍትሕንና ቅንነትንም፣ለያዕቆብ አደረግህ።

5 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፤በእግሩ መርገጫ ስገዱ፤እርሱ ቅዱስ ነውና።

6 ሙሴና አሮን ካህናቱ ከሆኑት መካከል ነበሩ፤ሳሙኤልም ስሙን ከጠሩት መካከል አንዱ ነበረ፤እነርሱ ወደ እግዚአብሔር ተጣሩ፤እርሱም መለሰላቸው።

7 ከደመና ዐምድ ውስጥ ተናገራቸው፤እነርሱም ሥርዐቱንና የሰጣቸውን ድንጋጌ ጠበቁ።

8 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤አንተ መለስህላቸው፤ጥፋታቸውን ብትበቀልም እንኳ፣አንተ ይቅር የምትላቸው አምላክ ነህ።

9 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፤በቅዱስ ተራራውም ላይ ስገዱ፤አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና።