መዝሙር 141 NASV

የክፉዎችን ድሎት ላለመመኘት የቀረበ ጸሎት

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤ ፈጥነህ ድረስልኝ፤ወደ አንተ ስጣራም ድምፄን ስማ።

2 ጸሎቴ በፊትህ እንደ ዕጣን ትቈጠርልኝ፤እጄን ማንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።

3 እግዚአብሔር ሆይ፤ ለአፌ ጠባቂ አድርግ፤የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ።

4 ከዐመፀኞች ጋር፣በክፉ ሥራ እንዳልተባበር፣ልቤን ወደ ክፉ አታዘንብል፤ከድግሳቸውም አልቋደስ።

5 ጻድቅ ሰው ይቅጣኝ፤ ይህ በጎነት ነው፤ይገሥጸኝም፤ በራሴ ላይ እንደሚፈስ ዘይት ነው፤ራሴም ይህን እንቢ አይልም።ጸሎቴ ግን በክፉዎች ተግባር ላይ ነው፤

6 ሹማምታቸው ከገደል አፋፍ ቍልቍል ይወረወራሉ፣ቃሌ የምታረካ ናትና፣ ይሰሟታል።

7 ደግሞም፣ “ሰው ምድርን እንደሚያርስና ዐፈሩን እንደሚፈረካክስ፣እንዲሁ ዐጥንታችን በሲኦል አፋፍ ላይ ተበታተነ” ይላሉ።

8 ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖቼ ግን ወደ አንተ ይመለከታሉ፤መጠጊያዬም አንተ ነህ፤ እንግዲህ ነፍሴን አትተዋት።

9 ከዘረጉብኝ ወጥመድ፣ከክፉ አድራጊዎችም አሽክላ ጠብቀኝ።

10 እኔ ብቻ በደኅና ሳመልጥ፣ክፉዎቹ በገዛ ወጥመዳቸው ይውደቁ።