መዝሙር 84 NASV

ወደ መቅደሱ ጒዞ መዝሙር

ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት የሚዜም የቆሬ ልጆች መዝሙር

1 የሰራዊት አምላክ ሆይ፤ማደሪያህ ምንኛ የተወደደ ነው!

2 ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትናፍቃለች፤እጅግም ትጓጓለታለች፤ልቤና ሥጋዬም፣ለሕያው አምላክ እልል በሉ።

3 ንጉሤና አምላኬ የሰራዊት አምላክ ሆይ፤መሠዊያህ ባለበት ስፍራ፣ድንቢጥ እንኳ መኖሪያ ቤት፣ዋኖስም ጫጩቶቿን የምታኖርበት ጐጆ አገኘች።

4 በቤትህ የሚኖሩ የተባረኩ ናቸው፤እነርሱም ለዘላለም ያመሰግኑሃል። ሴላ

5 አንተን ብርታታቸው ያደረጉ፣በልባቸው የጽዮንን መንገድ የሚያስቡ ቡሩካን ናቸው።

6 በልቅሶ ሸለቆ በሚያልፉበት ጊዜ፣የምንጭ መፍለቂያ ቦታ ያደርጉታል፤የበልጒም ዝናብ ያረሰርሰዋል።

7 ከኀይል ወደ ኀይል ይሸጋገራሉ፤እያንዳንዱም በጽዮን ባለው አምላክ ፊት ይቀርባል።

8 የሰራዊት አምላክ ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤የያዕቆብ አምላክ ሆይ አድምጠኝ። ሴላ

9 አምላክ ሆይ፤ ጋሻችንን እይልን፤የቀባኸውንም ተመልከት።

10 በሌላ ስፍራ ሺህ ቀን ከመኖር፣በአደባባይህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል፤በክፉዎች ድንኳን ከመቀመጥ ይልቅ፣በአምላኬ ቤት ደጅ መቆም እመርጣለሁ።

11 እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።

12 የሰራዊት አምላክ ሆይ፤በአንተ የታመነ ሰው ቡሩክ ነው።