መዝሙር 63 NASV

እግዚአብሔርን መፈለግ

በይሁዳ ምድረ በዳ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ሥጋዬም አንተን ናፈቀች።

2 ስለዚህ በመቅደስ ውስጥ አየሁህ፤ኀይልህንና ክብርህንም ተመለከትሁ።

3 ምሕረትህ ከሕይወት ይበልጣልና፤ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።

4 እንግዲህ፣ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፤በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ።

5 ነፍሴ በቅቤና በሥብ እንደሚረካ ሰው ትረካለች፤አፌም በሚያዜሙ ከንፈሮች በደስታ ያወድስሃል።

6 በመኝታዬ አስብሃለሁ፤ሌሊቱንም ሁሉ ስለ አንተ አሰላስላለሁ።

7 አንተ ረዳቴ ነህና፣በክንፎችህ ሥር ተጠልዬ በደስታ እዘምራለሁ።

8 ነፍሴ አንተን የሙጥኝ ብላለች፤ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች።

9 ነፍሴን ለማጥፋት የሚሹ ግን፣ወደ ምድር ጥልቅ ይወርዳሉ፤

10 ለሰይፍ አልፈው ይሰጣሉ፤የቀበሮዎችም ምግብ ይሆናሉ።

11 ንጉሥ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤በእግዚአብሔርም ስም ቃል የሚገቡ ሁሉ ይከብራሉ፤የሐሰተኞች አንደበትም ትዘጋለች።