መዝሙር 94 NASV

የእግዚአብሔር ፍትሕ

1 የበቀል አምላክ፣ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤የበቀል አምላክ ሆይ፤ ደምቀህ ተገለጥ።

2 አንተ የምድር ዳኛ ሆይ፤ ተነሥ፤ለትዕቢተኞች የእጃቸውን ስጣቸው።

3 ክፉዎች እስከ መቼ እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፉዎች እስከ መቼ ይፈነጫሉ?

4 የእብሪት ቃላት ያዥጐደጒዳሉ፤ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ጒራ ይነዛሉ።

5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አደቀቁ፤ርስትህንም አስጨነቁ።

6 መበለቲቱንና መጻተኛውን ገደሉ፤የድኻ አደጉንም ነፍስ አጠፉ።

7 እነርሱም “እግዚአብሔር አያይም፤የያዕቆብም አምላክ አያስተውልም” አሉ።

8 እናንት በሕዝቡ መካከል ያላችሁ ደነዞች፤ ልብ በሉ፤እናንት ቂሎች፤ ጥበበኞች የምትሆኑት መቼ ነው?

9 ጆሮን የተከለው እርሱ አይሰማምን? ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን?

10 ሕዝቦችን በተግሣጽ ወደ መንገድ የሚመልስ፣ዕውቀትንስ ለሰው ልጆች የሚያስተምር አይቀጣምን?

11 እግዚአብሔር የሰው ሐሳብ መና፣ከንቱም እንደሆነ ያውቃል።

12 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የምትገሥጸው፣ከሕግህም የምታስተምረው ሰው ምስጉን ነው።

13 ለኀጢአተኞች ጒድጓድ እስኪማስላቸው ድረስ፣እርሱን ከመከራ ታሳርፈዋለህ።

14 እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፤ርስቱንም አይተውም።

15 ፍርድ ተመልሶ በጽድቅ አሠራር ላይ ይመሠረታል፤ልባቸውም ቀና የሆነ ሁሉ ይከተሉታል።

16 ክፉዎችን የሚቋቋምልኝ ማን ነው?ከክፉ አድራጊዎችስ ጋር የሚሟገትልኝ ማን ነው?

17 እግዚአብሔር ረዳቴ ባይሆን ኖሮ፣ነፍሴ ወደ ዝምታው ዓለም ፈጥና በወረደች ነበር።

18 እኔ፣ “እግሬ አዳለጠኝ” ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ።

19 የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።

20 ዐመፃን ሕጋዊ የሚያደርግ፣የጥፋት ዙፋን ከአንተ ጋር ሊያብር ይችላልን?

21 በጻድቁ ላይ ተሰልፈው ይወጣሉ፤በንጹሑም ላይ ሞት ይፈርዳሉ።

22 ለእኔ ግን እግዚአብሔር ምሽግ፣አምላኬም መጠጊያ ዐለት ሆኖኛል።

23 በደላቸውን ወደ ራሳቸው ይመልሳል፤በክፋታቸውም ያጠፋቸዋል፤ እግዚአብሔር አምላካችን ይደመስሳቸዋል።