መዝሙር 140 NASV

በክፉዎች ላይ የቀረበ ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከክፉ ሰዎች አድነኝ፤ከዐመፀኞችም ሰዎች ጠብቀኝ፤

2 እነርሱ በልባቸው ክፉ ነገር ያውጠነጥናሉ፤በየዕለቱም ጦርነት ይጭራሉ።

3 ምላሳቸውን እንደ እባብ ያሾላሉ፤ከከንፈራቸውም በታች የእፉኝት መርዝ አለ። ሴላ

4 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከክፉዎች እጅ ጠብቀኝ፤እግሮቼንም ለመጥለፍ ከሚያደቡ ዐመፀኞች ሰውረኝ።

5 ትዕቢተኞች ወጥመድ በስውር አስቀመጡብኝ፤የመረባቸውን ገመድ ዘረጉብኝ፤በመንገዴም ላይ አሽክላ አኖሩ። ሴላ

6 እግዚአብሔር ሆይ፤ “አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የልመና ጩኸቴን ስማ።

7 ብርቱ አዳኝ የሆንህ፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤በጦርነት ዕለት የራስ ቍር ሆንኸኝ።

8 እግዚአብሔር ሆይ፤ የክፉዎች ምኞት አይፈጸም፤በትዕቢትም እንዳይኵራሩ፣ዕቅዳቸው አይሳካ። ሴላ

9 ዙሪያዬን የከበቡኝ ሰዎች ራስ፣የከንፈራቸው መዘዝ ይጠምጠምበት።

10 የእሳት ፍም በላያቸው ይውረድ፤ዳግመኛም እንዳይነሡ ወደ እሳት ይጣሉ፤ማጥ ወዳለበት ጒድጓድ ይውደቁ።

11 ምላሰኛ በምድሪቱ ጸንቶ አይኑር፤ዐመፀኛውን ሰው ክፋት አሳዶ ያጥፋው።

12 እግዚአብሔር ለድኻ ፍትሕን እንደሚያስከብር፣ለችግረኛውም ትክክለኛ ፍርድን እንደሚሰጥ ዐውቃለሁ።

13 ጻድቃን በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፤ቅኖችም በፊትህ ይኖራሉ።