መዝሙር 42 NASV

ሁለተኛ መጽሐፍ

በብዙ የዕብራይስጥ ቅጆች መዝሙር 42 እና 43 አንድ መዝሙር ነው።

በስደት ላይ ያለ ሌዋዊ ልቅሶ

1 ዋላ የምንጭ ውሃ እንደምትናፍቅ፣አምላክ ሆይ፤ ነፍሴም እንዲሁ አንተን ትናፍቃለች።

2 ነፍሴ አምላክን፣ ሕያው አምላክን ተጠማች፤መቼ ደርሼ ነው የአምላክን ፊት የማየው?

3 ሰዎች ቀኑን ሙሉ፣“አምላክህ የት አለ?” ባሉኝ ቍጥር፣እንባዬ ቀንና ሌሊት፣ምግብ ሆነኝ።

4 ነፍሴ በውስጤ እየፈሰሰች፣እነዚህን ነገሮች አስታወስሁኝ፤ታላቅ ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ቤት እየመራሁ፣በእልልታና በምስጋና መዝሙር፣በአእላፍ ሕዝብ መካከል፣እንዴት ከሕዝቡ ጋር እሄድ እንደ ነበር ትዝ አለኝ።

5 ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ?ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ?ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፤አዳኜና

6 አምላኬን፣ ገና አመሰግነዋለሁና።ነፍሴ በውስጤ ተክዛለች፤ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር፣በአርሞንኤም ከፍታ፣ በሚዛር ተራራ አስብሃለሁ።

7 በፏፏቴህ ማስገምገም፣አንዱ ጥልቅ ሌላውን ጥልቅ ይጣራል፤ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ፣ሙሉ በሙሉ አጥለቀለቀኝ።

8 እግዚአብሔር ምሕረቱን በቀን ያዝዛል፤ዝማሬውም በሌሊት በእኔ ዘንድ አለ፤ይህም ለሕይወቴ አምላክ የማቀርበው ጸሎት ነው።

9 እግዚአብሔር ዐለቴን፣“ለምን ረሳኸኝ?ጠላትስ እያስጨነቀኝ፣ለምን በሐዘን እመላለሳለሁ?” እለዋለሁ።

10 ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ፣“አምላክህ የት አለ?” እያሉ፣በነገር ጠዘጠዙኝ፣ዐጥንቴም ደቀቀ።

11 ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ?ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ?ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፣አዳኜና አምላኬን፣ገና አመሰግነዋለሁ።