1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ለምን እንዲህ ርቀህ ቆምህ?በመከራ ጊዜስ ለምን ድምፅህን አጠፋህ?
2 ክፉዎች የተጨነቀውን በእብሪት ያሳድዳሉ፤በወጠኑት ተንኰል ይጠመዱ።
3 ክፉ ሰው በልቡ ምኞት ይኵራራል፤ስግብግቡን ይባርካል፤ እግዚአብሔርንም ይዳፈራል።
4 ክፉ ሰው ከትዕቢቱ የተነሣ እግዚአብሔርን አይፈልግም፤በሐሳቡም ሁሉ አምላክ የለም፤
5 መንገዱ ዘወትር የተሳካ ነው፤ዕቡይ፣ ከሕግህም የራቀ ነው።በመሆኑም በጠላቶቹ ላይ ያፌዛል።
6 በልቡም፣ “ከስፍራዬ የሚነቀንቀኝ የለም፤ከትውልድ እስከ ትውልድም መከራ አያገኘኝም” ይላል።
7 አፉ መርገምን፣ ቅጥፈትንና ግፍን የተሞላ ነው፤ሽንገላና ክፋት ከምላሱ ሥር ይገኛሉ።
8 በየመንደሩ ሥርቻ ያደፍጣል፤ንጹሐንን በሰዋራ ስፍራ ይገድላል።ዐይኖቹንም በምስኪኖች ላይ ያነጣጥራል።
9 በደኑ ውስጥ እንዳለ አንበሳ በስውር ያደባል፤ረዳት የሌለውን ለመያዝ ያሸምቃል፤ድኻውንም አፈፍ አድርጎ በወጥመዱ ይጐትታል።
10 ምስኪኑም ይደቃል፤ ዐንገቱን ይደፋል፤ያልታደለውም በክንዱ ሥር ይወድቃል።
11 በልቡም፣ “እግዚአብሔር ረስቶአል፤ፊቱን ሸፍኖአል፤ ፈጽሞም አያይም”ይላል።
12 እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ፤ አምላክ ሆይ፤ ክንድህን አንሣ፤ረዳት የሌላቸውንም አትርሳ።
13 ክፉ ሰው በእግዚአብሔር ላይ ለምን ክፉ ይናገራል?በልቡስ፣ “ስለ ሥራዬ አይጠይቀኝም”ለምን ይላል?
14 አንተ ግን መከራንና ሐዘንን ታያለህ፤በእጅህም ዋጋ ለመክፈል ትመለከታለህ፤ምስኪኑም ራሱን በአንተ ላይ ይጥላል፤ለድኻ ዐደግም ረዳቱ አንተ ነህ።
15 የክፉውንና የበደለኛውን ክንድ ስበር፤የእጁንም ስጠው፤ምንም እስከማይገኝ ድረስ።
16 እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ነው፤ሕዝቦችም ከምድሩ ይጠፋሉ።
17 እግዚአብሔር ሆይ፤ የተገፉትን ምኞት ትሰማለህ፤ልባቸውን ታበረታለህ፤ ጆሮህንም ወደ እነርሱ ጣል ታደርጋለህ፤
18 ከዐፈር የተፈጠረ ሰው ከእንግዲህእንዳያስጨንቃቸው፣አንተ ለድኻ ዐደጉና ለተገፋው ትሟገታለህ።