መዝሙር 51 NASV

የኀጢአት ኑዛዜ

ለመዘምራን አለቃ፤ ዳዊት ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ፣ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ምሕረት አድርግልኝ፤እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣መተላለፌን ደምስስ።

2 በደሌን ፈጽሞ እጠብልኝ፤ከኀጢአቴም አንጻኝ።

3 እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፤ኀጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው።

4 በውሳኔህ ትክክል፣በምትሰጠው ፍርድም ንጹሕ ትሆን ዘንድ፣አንተን፣ በእርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ፤በፊትህም ክፉ ነገር አደረግሁ።

5 ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ።

6 እነሆ፤ እውነትን ከሰው ልብ ትሻለህ፤ስለዚህ ጥልቅ ጥበብን በውስጤ አስተምረኝ።

7 በሂሶጵ እርጨኝ፤ እኔም እነጻለሁ፤እጠበኝ፤ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።

8 ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፤ያደቀቅሃቸው ዐጥንቶቼም ደስ ይበላቸው።

9 ፊትህን ከኀጢአቴ መልስ፤በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።

10 አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።

11 ከፊትህ አትጣለኝ፤ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ።

12 የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ።

13 እኔም ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ፤ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።

14 የድነቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤አንደበቴም ስለ ጽድቅህ በእልልታ ይዘምራል።

15 ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤አፌም ምስጋናህን ያውጃል።

16 መሥዋዕትን ብትወድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም።

17 እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤እግዚአብሔር ሆይ፤አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።

18 በበጎ ፈቃድህ ጽዮንን አበልጽጋት፤የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች ሥራ።

19 የጽድቅ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና፣ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያን ጊዜ ደስ ያሰኙሃል፤ኮርማዎች በመሠዊያህ ላይ የሚሠዉትም ያን ጊዜ ነው።