መዝሙር 46 NASV

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር፤ በደናግል የዜማ ስልት የሚዘመር፣ መዝሙር።

1 አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን፣በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው።

2 ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ እንኳ፣ተራሮችም ወደ ባሕር ጥልቅ ቢሰምጡ አንፈራም።

3 ውሆች ቢያስገመግሙ፣ ዐረፋ ቢደፍቁም፣ ተራሮችም ከውሆቹ ሙላት የተነሣቢንቀጠቀጡም አንደናገጥም። ሴላ

4 የእግዚአብሔርን ከተማ፣የልዑልን የተቀደሰ ማደሪያ ደስ የሚያሰኝ የወንዝ ፈሳሾች አሉ።

5 እግዚአብሔር በመካከሏ ነው፤ አትናወጥም፤አምላክ በማለዳ ይረዳታል።

6 ሕዝቦች በዐመፅ ተነሡ፤ መንግሥታትም ወደቁ፤ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰማ፤ ምድርም ቀለጠች።

7 የሰራዊት አምላክ ከእኛ ጋር ነው፤የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው። ሴላ

8 ኑና የእግዚአብሔርን ሥራ፣ምድርንም እንዴት ባድማ እንዳደረጋት እዩ።

9 ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል።

10 “ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደሆንሁ ዕወቁ፤በሕዝቦች ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፤በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።”

11 የሰራዊት አምላክ ከእኛ ጋር ነው፤የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው። ሴላ