መዝሙር 17 NASV

የንጹሕ ሰው አቤቱታ

የዳዊት ጸሎት

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅንነት የቀረበውን አቤቱታዬን ስማ፤ጩኸቴንም አድምጥ፤ከአታላይ ከንፈር ያልወጣውን፣ጸሎቴን አድምጥ።

2 ጽድቄ ከአንተ ዘንድ ይምጣ፤ዐይኖችህም ፍትሕን ይዩ።

3 ልቤን መረመርኸው፣ በሌሊት ጠጋብለህ ፈተንኸኝ፤ፈተሽኸኝ አንዳች አላገኘህብኝም፤አንደበቴም ዕላፊ አልሄደም።

4 ከሰዎች ተግባር፣በከንፈርህ ቃል፣ከዐመፀኞች መንገድ፣ራሴን ጠብቄአለሁ።

5 አረማመዴ በመንገድህ ጸንቶአል፤እግሮቼም አልተንሸራተቱም።

6 አምላክ ሆይ፤ ስለምትመልስልኝ አንተን እጣራለሁ፤ጆሮህን ወደ እኔ ጣል አድርገህ ጸሎቴን ስማ።

7 ከጠላቶቻቸው መተገኛ ያደረጉህን፣በቀኝ እጅህ የምትታደግ ሆይ፤ጽኑ ፍቅርህን ድንቅ አድርገህ ግለጥ።

8 እንደ ዐይንህ ብሌን ጠብቀኝ፤በክንፎችህም ጥላ ሰውረኝ፤

9 ከሚያስጨንቁኝ ከክፉዎች፣ከሚከብቡኝ አደገኛ ባላንጣዎቼ ጋርደኝ።

10 ደንዳና ልባቸውን ደፈኑት፤በአፋቸውም ትዕቢት ይናገራሉ።

11 አሳደው ደረሱብኝ፤ ከበቡኝም፤መሬት ላይ ሊዘርሩኝም አፈጠጡብኝ።

12 እነርሱ ለንጥቂያ እንደሚጓጓ አንበሳ፣በስውርም እንደሚያደባ ደቦል አንበሳ ናቸው።

13 እግዚአብሔር ሆይ፤ ተነሥተህ ግጠማቸውና ጣላቸው፤በሰይፍህም ከክፉዎች ታደገኝ።

14 እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲህ ካሉት ሰዎች በክንድህ አድነኝ፤ዕድል ፈንታቸው ይህችው ሕይወት ብቻ ከሆነች፣ ከዚህ ዓለም ሰዎች ታደገኝ።ከመዝገብህ ሆዳቸውን ሞላህ፤ልጆቻቸውም ተትረፍርፎላቸዋል፤ለልጆቻቸውም ሀብት ያከማቻሉ።

15 እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ስነቃም ክብርህን አይቼ እረካለሁ።